ለችግሮቻቸው አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሹ በምስራቅ ወለጋ ዞን በመጠለያ የሚገኙ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ተፈናቃዮች

58
ነቀምቴ ጥቅምት 24/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች በተፈጠረው ግጭት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቅሉ ወገኖች ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠየቁ። በምስራቅ ወለጋ ዞን በየመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች መንግሥት በአፋጣኝ ለደረሰባቸው ችግር ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጥበት ይገባል ብለዋል ከተፈናቃዮቹ መካከል ከያሶ ወረዳ የተፈናቀሉ አቶ አያና ጉዳታ የተባሉ የመንግሥት ሠራተኛ እንደገለጹት ከመስከረም 15/2011 ዓ.ም ጀምሮ በተፈጸመ ጥቃት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በሐሮ ሊሙ መጠለያ ጣቢያ ይገኛሉ፡፡ ከተፈናቃዮቹ መካከል 183 የመንግስት ሰራተኞች የሁለት ወር ደሞዝ ስላልተከፈላቸው ከነቤሰተቦቻቸው ችግር ላይ መውደቃቸውንም አስታውቀዋል። ለችግሩ መንግሥት አስፈላጊውን መፍትሄ እንዲሰጣቸው የከያሶ፣ካማሺ፣አገሎ፣ስርባ አባይ፣እና ከበሎጀገንፎኢ ወረዳዎች የተውጣጡ ተፈናቃዮችን በመወከል እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በማመልከት መፍትሔ እየጠበቁ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ አሁንም ቢሆን የተፈናቀሉበት ካማሺ ዞን ሰዎች በግፍ እየተንገላቱ የሚገኙበት በመሆኑ  በዞኑ አስተማማኝ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን መንግስት በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል። "ሕገ-ወጥ ትጥቅን በማስፈታትና አጥፊዎቹን ለሕግ በማቅረብ እኛ ተፈናቃዮቹን በአስቸኳይ ወደ ቀያችን ሊመልሰን ይገባል” ሲሉ ጠይቀዋል። ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በተደጋጋሚ በአካባቢው እየደረሰ ያለው መፈናቀልና የመብት ረገጣ የተለመደ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ከያሶ ወረዳ ከሀሎ ሙከርባ ቀበሌ ከ5 ከቤተሰባቸው ጋር እንደተፈናቀሉ የተናገሩት አርሶ አደር ጌታቸው ፀጋዬ ናቸው፡፡ ማምለጥ ባልቻሉት ዜጎች ላይ አስከፊ ጉዳት እየደረሰ በመሆኑ ስጋት እንዳደረባቸው ገልጸው ሰላም ሰፍኖ ወደ ቤታቸው ተመልሰው መደበኛ ኑሯቸውን መግፋት እንዲችሉ መንግስት ሁኔታዎችን እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል። ለችግሩ ምንስዔ ናቸው የተባሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ለሕግ በመጠየቅ ለወደመው የሕዝብ ሀብትና ንብረት የዞኑ አመራሮች ተጠያቂ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የመንግስት ሰራተኛዋ ወይዘሮ አስቴር ገርቢ ናቸው፡፡ የሐሮ ሊሙ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሮማ ቶለሣ በበኩላቸው በወረዳው ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች ቁጥር ከ38 ሺህ 400 በላይ መድረሱንና መፈናቀሉ አሁንም ባለመቆሙ በየቀኑ ወደ ወረዳው የሚገባው ሰው መጨመሩን ገልጸዋል። የምሥራቅ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገመቺስ ተመስጌን ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው የሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም