“የተምታታው ስፖርት እና ፖለቲካ”

2008

ነጻነት አብርሃም /ኢዜአ/

እግር ኳስ መዝናኛ፣ ጊዜ ማሳለፊያ ወይስ የፖለቲካና የብሄር መልእክት ማስተላለፊያ? ትርጉሙ የትኛው ይሆን? በአሁኑ ወቅት የአገራችን እግር ኳስ እነዚህና የመሳሰሉት ትርጓሜዎች እየተሰጡት ለዛውን እያጣ የመጣ ይመስላል። በዓለማችን አዝናኝና አስደሳች ከሚባሉ እንዲሁም በብዙ የስፖርት ቤተሰቦች ዘንድም ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ስፖርታዊ ክንውኖች መካከል እግር ኳስ ቀዳሚ ስለመሆኑ አያጠያይቅም። እግር ኳስ በተለይም በምዕራባዊያን ዘንድ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ የእድገት ግስጋሴው ዘላቂ በሚባል ደረጃ ላይ መሆኑንም እንመለከታለን ።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንደ አዲስ ከተመሰረተ እነሆ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የሆነ ጊዜን አስቆጥሯል። በፕሪሚየር ሊጉ የሚሳተፉ ክለቦች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና ወደ ኳስ ሜዳ ጨዋታዎችን ለመከታተል የሚተሙ ተመልካቾች ቁጥርም እየናረ መጥቷል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፈዴሬሽን ከሚያካሂዳቸው ውድድሮች መካከል ፕሪሚየር ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግ (ሱፐር ሊግ) እና ብሔራዊ ሊግ በዋናነት የሚጠቀሱ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በፕሪሚየር ሊጉ 16 ክለቦች ይሳተፋሉ።

ይሁን እንጂ የሊጉ ተሳታፊ ክለቦች በአገር ውስጥ ከሚያደርጉት የእርስ በርስ ሹኩቻ ባሻገር በዓለም አቀፍም ሆነ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ያለው ውጤት እዚህ ግባ የማይባል ስለመሆኑም የአደባባይ ሃቅ ነው።

በአንጻሩ ደግሞ ስፖርታዊ ውድድሮች የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነት፣ የአንድነትና የወንድማማችነት መድረክ ስለመሆናቸውና ፤ ስለ ስፖርታዊ ጨዋነትና የእግር ኳስ ደጋፊዎች ስነ-ምግባር በተለያዩ ጊዜያት እየተነገረ ቢሆንም አሁንም ድረስ ግን ጉንጭ ከማልፋት የዘለለ ለውጥ የማምጣቱ ነገር ለሁሉም የስፖርት ቤተሰብ ራስ ምታት ሆኗል።

አሁን አሁን አንዳንድ የእግር ኳስ ፍቅር ከልብ ያልገባቸውና ስፖርትና ፖለቲካ የተምታታባቸው ስፖርት ወዳድ ደጋፊዎች ነን ባዮች በእግር ኳስ ሜዳ ላይ አላስፈላጊ ተግባር ሲፈጽሙ ብሎም የሌሎችን ክብርና ነፃነት የሚጋፋ መልእክቶችና ፖለቲካዊ ተቃውሞዎች ሲያስተላልፉ እንዲሁም አላስፈላጊ ጠብ እና ግጭት የሚያጭሩ ክስተቶችን ሲያስተናግዱም ይስተዋላል።

ምንም እንኳን በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ደጋፊዎች ሲበሻሻቁና የራሳቸውን ክለብ እያሞገሱ የሌላውን ሲያጣጥሉ ማየት የተለመደ ቢሆንም ከዚህም አልፎ ተርፎ ነገ ለትውልድ የሚተላለፉና የሚጠቅሙ መቀመጫ ወንበሮችን እየነቀሉና እየሰበሩ በአላስፈላጊ መልኩ ሲጎዳዱ በደጋፊዎች ላይም ጉዳት ሲደርስ ማየትም የተለመደ እየሆነ መጥቷል።

እንደእኔ እምነት ይህ ከጊዜ በኋላ የመጣ ስርዓት አልበኝነትና ስፖርታዊ ጨዋነት የጎደለው ድርጊት እግር ኳሳዊ ፉክክሩ ከመዝናኛነቱ ባሻገር ዘረኝነት በሚንጸባረቅባቸው ሁነቶች ፖለቲካዊ አንድምታው ጎልቶ እየታየ የመጣ ይመስለኛል። በዚህም በደጋፊዎች መካከል ለሚቀስቀስ ግጭትና ትርምስ ምክንያት በሚፈጠር ሁከትም ከስፖርታዊ ክንውኑ ባሻገር ሰብአዊነት በጎደላቸው ተግባራት በስፖርት ሜዳ ላይ የሰው ልጅ ህይወት አለአግባብ ሲጠፋና አካል ሲጎዳም እየተመለከትን እንገኛለን።

ለአብነት የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ግጭቶችና ረብሻዎች የተበራከቱበት፣ ዳኞች በአደባባይ የተደበደቡበትና በአጠቃላይ ከፍተኛ ስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት የነበረበት እንደነበር ማስታወስ ይቻላል። በክልሎች ጨዋታ ማድረግ ለክለቦችና ለተጨዋቾች እንዲሁም ለደጋፊዎችም አስቸጋሪ የሆነበትም ጭምር እንደነበር ማስታወስ ይቻላል።

በወልዲያ ስፖርት ክለብ እና በመቀሌ ከተማ መካከል ሊደረግ የነበረው የእግር ኳስ ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ በደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ለሰው ልጅ ህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ምክንያት ነበር። ይህም አላስፈላጊ ድርጊትና ክስተት በስፖርት ቤተሰቦች ላይ ሁሉ የንዴትና የሃዘን ስሜት የፈጠረ ስለመሆኑም አያጠያይቅም።

ታዲያ ይህ ስርዓት አልበኝነት በአገራችን ያላደገውንና ዳዴ የሚለውን እግር ኳስ ወደኋላ የሚያስቀር ከመሆኑም ባሻገር እነዚህ በባህል፣ በታሪክ፣ በኃይማኖት፣ በቋንቋና በደም የተሳሳሩና አንድ የሆኑትን ህዝቦች የሚያራርቅ ብሎም ኢትዮጵያ በአለም የምትታወቅበትን እርስ በርስ ተባብሮና ተከባብሮ የመኖር ባህሏንና መልካም ገጽታዋን የሚያጠለሽ መሆኑን ታዲያ ስለምን ማሰብ ተሳነን?

ኢትዮጵያ በቀደመ ታሪኳ በስፖርቱ መድረክ አፍሪካዊያን ነፃነታቸውን እንዲቀዳጁና ከጭቆናና ከባርነት ቀንበር እንዲላቀቁ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ ያሰማች አገር መሆኗ እሙን ነው። በዓለም አቀፍ መድረክም ስፖርት ከዘረኝነትና ከአድሎ የፀዳ የሰላምና የፍቅር መድረክ እንዲሆንም በጽኑ የታገለች አገር መሆኗንም እንዲሁ። እንደእነ ይድነቃቸው ተሰማ ያሉ የአፍሪካ የእግር ኳስ አባትና መስራች፤ ስፖርቱ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነት፣ የአንድነት፣ የወንድማማችነት፣ የትብብርና የሌሎችም መልካም ተግባራት መገለጫ እንዲሆን ጸንተው የሰሩና የታገሉ መሆናቸውንም ማስታወስ ግድ ይለናል።

ስፖርት በዓለም አቀፉ መድረክ ሁሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነትና የአንድነት፣ የመተሳሰብ፣ የወንድማማችነት ልዩ መገለጫ ነው፤ የሌሎች መልካም ተግባራትም ጭምር። በርካታ የታሪክ ድርሳናትና ጸሃፍት፤ ስፖርት በአለም መድረክ ላይ ስላለው ትልቅ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ይመሰክራሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የአለም አገሮችን ድንበር ተሻግሮ የዘር፣ የጎሳና የኃይማኖት ልዩነቶች ሳይገድበው የዓለም ቋንቋ መሆን እንደሚችልም እሙን ነው። ስፖርት ሲኖር የፍቅር ዜማ በአንድነት ይዘመራል፤ ስፖርት ሲያድግ የአገርና የህዝቡ ስልጣኔ እየጨመረና እያደገም ይመጣል።

ለዚህም አበይት ምሳሌ እንዲሆን ዘንዳ:- የጥቁር ህዝቦች የነጻነት አባት ኔልሰን ማንዴላ በአፓርታይዳዊ ስርዓት ምክንያት የተቃረነውንና ሰላም የራቀውን ደቡብ አፍሪካዊ ህዝብ አንድ ያደረጉት “የራግቢ” ስፖርትን ተጠቅመው እንደነበር የታሪክ መዛግብት ይተርካሉ።

በሌላ መልኩ ኔልሰን ማንዴላ በዓለም አቀፉ የስፖርት መድረክ ለሰው ልጆች ነፃነትና መብት ባደረጉት ትግል፤ በተሰጣቸው ዓለም አቀፍ ሽልማት ስለ ስፖርት እንዲህ ሲሉ ተናግረው ነበር ፦ “Sports had the power to change the world … to inspire … to unite people. “(ስፖርት ዓለምን ለመቀየር እና  የሰው ልጆችን ሁሉ አንድ የሚያደርግ መሳሪያ ነው)።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባንኪሙን እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ግንቦት 11 ቀን 2011 በስዊዘርላንድ ጄኔቫ “ስፖርት ለሰላምና ለልማት ያለው አስተዋጽዖ”  በሚል በተዘጋጀው መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግራቸው ስለ ስፖርት እንዲህ ብለው ነበር ፦

“Sport has become a world language, a common denominator that breaks down all the walls, all the barriers. It is a worldwide industry whose practices can have a widespread impact. Most of all, it is a powerful tool for progress and development.” (ስፖርት የዓለም ቋንቋ ነው፤ ስፖርት ሁሉንም ግድግዳና መስናክሎች የመደርመስ አቅም ያለው ዓለም አቀፍ ተጽእኖ ማሳደር የሚችል ኢንዱስትሪ ጭምር ብቻ ሳይሆን በልማት ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና ያለው ነው)”።

እንደሚታወቀው እግር ኳስ አለም ላይ በርካታ ተመልካች ያለውና የሚወደድ ስፖርታዊ ክንውን ቢሆንም እንኳን አልፎ አልፎ በአለም መድረክም ቢሆን በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ሁከትና ብጥብጥ መፈጠሩ አይቀሬ ነው። በዚህ ላይ አለም ፈጽሞ የማይረሳውና በርካታ የስፖርት ቤተሰቦችን ያስነባው የእግር ኳስ ክስተት በጥቂቱ ላስታውሳችሁ ወደድኩ።

ነገሩ እንዲህ ነው፤ጊዜው እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ሜይ 29 ቀን 1985 በአውሮፓ ክለቦች የፍጻሜ ጨዋታ በቤልጄም “ሄልስ” ስታዲየም የተደረገው የመርሲሳይዱ ክለብ ሊቨርፑልና የግሪኩን ፓናቲያኮስ ጁቬንቱስን ያገናኘ ነበር። ጨዋታውን ለመመልከትና ክለቦቻቸውን ለመደገፍ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በማቅናት የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎችና የሌሎችም አገራት ዜግነት ያላቸው የአለም ህዝቦችን ጨምሮ 58 ሺህ የሚሆኑ ታዳሚያን በስታዲየሙ ታጭቀዋል።

ይህ አለም በጉጉት የሚጠብቀው ጨዋታ እንደተጠበቀው በመልካም ድርጊቶች የታጀበ አልነበረም።  ውድድሩ ሊጀመር አንድ ሰዓት ያክል ቀርቶታል ይሁንና ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ በአንድ የሊቨርፑል ነውጠኛ ደጋፊ ምክንያት ሁከት ተፈጠረ፤ ይህም ቀጥሎ በደጋፊዎች መካከል ጠርሙስ በመወራወር የተጀመረው ግጭት አይሎ በርካታ ታዳጊ ህጻናትን ጨምሮ በእድሜ የገፉ ሰዎች ከአደጋው ለመሸሽ ሲሮጡ መደራረብ ተፈጠረ፤ የስታዲየሙ ክፍል ግድግዳም ተደርምሶ ወደቀ፤ በእለቱ የሚወዱትን እግር ኳስ ለመታደም አገር አቋርጠው በስታዲየሙ ከዘለቁ ደጋፊዎች መካከልም 32 ኢጣልያዊያን የጁቬንቱስ ደጋፊዎች፣ አራት ቤልጄማዊያን እና ሌሎች ፈረንሳያዊያንን ጨምሮ 39 የሚሆኑ ደጋፊዎች ህይወታቸው አለፈ። ከ600 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ለጉዳት ተዳረጉ። ጊዜው እግር ኳስ ፈጽሞ በታሪኩ አይቶት የማያውቀውን የስታዲየም ግጭትና ትስምስ፣ ሞትና ጉዳት አስተናገደ።

እንዲህ ያለው አላስፈላጊና ከስፖርታዊ ጨዋነት ያፈነገጠ ስርዓት አልበኝነት አሁን ላይ ደግሞ ወደ አገራችን እግር ኳስ በተለያዩ መልኩ እየመጣና እየተመለከትን መምጣቱም የአደባባይ ሃቅ ነው።

እንደ እኔ እምነት ማንኛውም የስፖርት ቤተሰብ ውድድሮችን በነጻነትና በሰላማዊ መንገድ በየትኛውም አካባቢ ላይ ተመልክቶና ተዝናንቶ ወደ ቤቱ የመግባት መብቱ ሊረጋገጥለት ይገባል።

የእግር ኳስ ፍቅር በማይገባቸው፣ በእግር ኳስ ሜዳ ላይ አላስፈላጊ ድርጊት በሚፈጽሙና ሁከት በሚፈጥሩ እግር ኳስ ወዳድ ተመልካች ነን ባይ አጥፊዎች ላይ ደግሞ ከጥፋታቸው እንዲታቀቡ ለማድረግ ከፌዴፌሽኑ ቅጣት በላይ የክለቦች ተቀራርቦ የመስራትና ደጋፊዎቻቸውን የማስተማሩ ተግባር ቀዳሚ መሆን ያለበት ይመስለኛል።

የዘንድሮ ፕሪሚየር ሊግም “ወራጅ ባህርያት” ሊኖሩት፣ ፍጹም በስፖርታዊ ጨዋነት የተሞላ፣  ፍጹም ሰላም የሰፈነበት፣ ከሁከትና ከረብሻ የራቀ፣ ደጋፊዎች የማይጎዱበት፣ የማይቆስሉበትና የማይሞቱበት እንዲሆንም ምኞቴ ነው።