የተጀመረው የተቋማት አደረጃጀት ማሻሻያ ሀብትን በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስችል ምሁራን ገለጹ

76
ነቀምቴጥቅምት 24/2011 በሀገሪቱ የተጀመረው የተቋማት አደረጃጀት ማሻሻያ ለውጥ ሀብትንና በጀትን  በአግባቡ ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ምሁራን ገለጹ፡፡ ከምሁራኑ መካከል በኦሮሚያ አቃቤ ሕግ ቢሮ የምዕራብ ችሎት ዓቃቤ ሕግ አቶ ደረጀ አበበ እንዳሉት የመንግሥት ተቋማት በሚደራጁበት ጊዜ የሕዝብ አገልግሎትን ማዕከል  በማድረግ መሆኑ ተገቢ ነው፡፡ ይህም ተደራራቢ ሥራን እንደሚቀንስና  ሀብትን ለመቆጠብ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡ የተጀመረው የተቋማት አደረጃጀት ማሻሻያ ለውጥ ስራዎችን  ከማጠናክር ባለፈ የተሾሙ ሰዎች በዝተው ሀብትን ያለ አግባብ  ከመጠቀም ያድናል የሚል እምነት እንዳላቸው አመልክተዋል፡ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና የሥራ አመራር ዳይሬክተር  ዶክተር ቀዲዳ ሶንቶ በበኩላቸው የተቋማት አደረጃጀት ማሻሻያ መካሄዱ   ያለ አግባብ ሲባክን የቆየው የሀገሪቱ ሀብትና የሰው ኃይልን  ውጤታማ በሆነ መልኩ መጠቀም እንደሚያስችል  ተናግረዋል፡፡ ምሁሩ እንዳመለከቱት ሥራዎች በየቦታው ተበታትነው መገኘታቸው የሀገሪቱን ሀብትና የተማረ የሰው ኃይል በአግባቡ መጠቀሙ ላይ አሉታዊ ተጽህኖ ያሳድራል፤ ሀብትን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ያስቸግራል፡፡ የአደረጃጀት ለውጡ ሰዎችን ከሥራ ያፈናቅላል የሚለው አስተሳሰብ አግባብ  እንዳልሆኑ ተናግረው የተቋማት መዋሃድ  ሀብትንና የሰው  ኃይሉን  በተመጣጠነ ሁኔታ  ለመምራት  እንደሚያስችል  ተናግረዋል፡፡ መንግስትም የጀመረውን የተቋማት አደረጃጀት ማሻሻል አጠናክሮ  ብቁ ባለሙያዎችን  በመመደብ በሀገሪቱ አጥጋቢና ውጤታማ ሥራዎችን እውን ማድረግ እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል፡፡ በሀገሪቱ የተጀመረው የተቋማት ማሻሻያ በበጀትና ሀብት አጠቃቀም ላይ የነበረውን  ጫና ለመቀነስና ቆጥቦ በአግባቡ ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ዘላለም እጅጉ ናቸው፡፡ የተበታተኑ ስራዎችን ወደ አንድ ሰብሰብ ባለ አካባቢ በማምጣት ውጤታማ ሥራን ለማሳካት ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ለውጡ መጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ አዲሱ የተቋማት አደረጃጀት የሚፈለገውን  የተማረ የሰው ኃይል ሊያጡና  ባለሙያዎች ከሙያቸው ውጭ ሊመደቡና በዚህም የሥራ ጫናዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ዶክተር ዘላለም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም