በአዲስ አበባ በህጻናት ማሳደጊያ ለሚገኙ ታዳጊዎች የስነ-ልቦና ስልጠና ተሰጠ

108
አዲስ አበባ ጥቅምት 24/2011 በአዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ በህጻናት ማሳደጊያ የሚገኙ ታዳጊዎች የስነ-ልቦና ስልጠና ተሰጣቸው። በስልጠናው ዕድሜያቸው ከዘጠኝ እስከ 18 ዓመት ያሉ 200 ታዳጊዎች የተሳተፉ ሲሆን ከቀጨኔ መድኃኔዓለም እና ኮልፌ ህጻናት ማሳደጊያ ማዕከላት የተውጣጡ ናቸው። ስልጠናው ህልምን እንዴት ማሳካት ይቻላል?፣ ራዕይ እንዳይሳካ የሚያደርጉ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? እንዴት የተሻለና ስኬታማ ሰው መሆን ይቻላል በሚሉ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠነ ሲሆን ከስኬታማ ግለሰቦች ታሪክና ልምድ እንዲማሩም ገለጻ ተደርጎላቸዋል። በአዲስ አበባ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ የህጻናት ድጋፍ ኢኒስፔክሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ገነት ጴጥሮስ እንደሚሉት፤ የስልጠናው ዓላማ የነገ አገር ተረካቢ ህጻናት ተስፋን እንዲሰንቁ ማድረግ ነው። ''በመዲናዋ ባሉ የህጻናት ማሳደጊያ ማዕከላት የምግብ፣ የጤናና የስነ ልቦና ድጋፍ ይሰጣል'' ያሉት ዳይሬክተሯ ድጋፉ ውጤታማ የሚሆነው የታዳጊዎቹ አመለካከት ሲቀየር ነው፤ በዚህ በኩል መሰል ስነ-ልቦናን የሚያጎለብቱ ስልጠናዎች ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል ይላሉ። በተለይ ታዳጊዎቹ ለውጥ አመጣለሁ፣ ሚና አለኝ ስኬታማ መሆን እችላለሁ የሚል አስተሳሰብ እንዲያጎለብቱ ማስቻል ሌላው የስልጠናው ዓላማ መሆኑን ነው የጠቀሱት። ስልጠናቅ ቀጣይነት እንደሚኖረው ጠቁመው ታዳጊዎቹ ወደፊት በሚኖራቸው ህይወት ውጤታማ እንዲሆኑ ማህበረሰቡ መደገፍ እንዳለበትም አሳስበዋል። ከሰልጣኞቹ መካከል ታዳጊ በለጡ ዓለምአየሁ የስልጠናው ተካፋይ በመሆኗ መደሰቷን ገልጻ ''ሁሉም ነገር በዓላማና በጥረት ከተደገፈ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ተገንዝቤአለሁ'' ብላለች። ተስፋን መሰነቋን የምትናገረው ታዳጊዋ ''የተሻለ ህይወት ይኖረኛል የሚል ተስፋን ይዤያለሁ ስትል ነው አስተያየቷን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጠችው። ሌላዋ ታዳጊ ሄለን ታደሰ በሰጠችው አስተያየት ''ከዚህ በፊት ቶሎ ተስፋ የምቆርጥ ሰው ነበርኩ፤ ትምህርቴን እንኳን አቋርጨ ነው የቀጠልኩት አሁን ግን ያለምኩትን ነገር ማሳካት እንዳለብኝ ተገንዝብያለሁ'' የሚል ሀሳብ አካፍላናለች። ''በፊት ያልነበረኝንና የማላስባቸውን ነገሮች በስልጠናው አግኝቻለሁ፤ ለራሴ ያለኝ ግምትም ከፍ ብሏል ያለችው ደግሞ ወጣት ዝናሽ ተስፋዬ ናት። ለታዳጊዎች ስልጠና የሰጡት ባለሙያ አቶ ዳዊት ድሪምስ በበኩላቸው ''ማንኛውም ሰው ግልጽና ትልቅ ህልም ሊኖረው ይገባል'' ይላሉ። ለታዳጊዎቹ የተሰጠው ስልጠና የወደፊት ህይወታቸውን መቀየር እንዲችሉ መሰረት የሚጥል መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያው ያላቸውንም እምቅ አቅም እንዲጠቀሙ የሚረዳ እንደሆነ አመልክተዋል። ተዳጊዎቹ በቀጣይ መሰል ድጋፍ ካገኙ ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጠቃሽ ዜጎች መሆን እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም