የትራፊክ አደጋን በመከላከሉ ዙሪያ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ብዙ መስራት ይጠይቃል

72
አዲስ አበባ  ጥቅምት 24/2011 በአዲስ አበባ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ቢሆንም የአደጋውን መጠን መቀነስ አልተቻለም። የከተማዋ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አደጋውን ለመቀነስና ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በርካታ ስራዎች ይጠበቁብኛል ይላል። በትራፊክ አደጋ ሳቢያ የሚከሰተው ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት እየጨመረ ሲሆን ችግሩን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ተጨባጭ ውጤት አልተገኘም። በ2011 በጀት ዓመት ሶስት ወራት በአዲስ አበባ 113 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን ማጣታቸውን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የመዲናዋ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ታመነ በሌ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ከኤጀንሲው የሚጠበቁ ስራዎች መኖራቸውን ይገልጻሉ። የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ከአሽከርካሪዎች ስነ-ምግባር፣ ከመንጃ ፈቃድ አሰጣጥና ከመንገድ መሰረተ ልማቶች ጋር የተያያዙ ከኤጀንሲው ቁጥጥር ውጭ የሆኑ ጉዳዮች ቢኖሩም ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስደው ኤጀንሲው በመሆኑ ብዙ ስራዎች ይጠበቁበታል ብለዋል። አቶ ታመነ እንደገለጹት በመዲናዋ የትራፊክ መሰረተ ልማት ባልተሟላበትና ለእግረኞች ምቹ መንገዶች በሌሉበት ሁኔታ የትራፊክ አደጋ በመቀነሱ በኩል ተጨባጭ ለውጥ ተገኝቷል ማለት አይቻልም። በመሆኑም ኤጀንሲው ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ከገባ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ነው የገለጹት። ለትራፊክ አደጋ አንዱ መንስኤ በፍጥነት ማሽከርከር ሲሆን የፍጥነት መቆጣጠሪያዎች በበቂ መጠን ባለመሰራታቸው የትራፊክ አደጋን መቀነስ አለመቻሉን ተናግረዋል። በተደጋጋሚ የትራፊክ አደጋ የደረሰባቸውና የተለዩ አካባቢዎች ላይ ከ90 በላይ የፍጥነት መገደቢያዎችና 70 የመኪና ማንቂያዎች ተሰርተዋል። በተያዘው በጀት አመት ደግሞ በሌሎች በተለዩ አካባቢዎች ላይ እየተከናወኑ እንደሚገኙ አቶ ታመነ ገልጸዋል። የእግረኛ ማቋረጫ ምልክቶች ያለመኖር ለአደጋ ትልቅ መንስኤ መሆኑን በመለየት ምልክቶች እየተሰሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። የትራፊክ መብራቶችና የመንገድ መገጣጠሚያ ምልክቶች ተከላ 305 ሚሊዮን ብር በመመደብ እየተከናወነ እንደሚገኝም አክለዋል። እንደ አቶ ታመነ ገለጻ የፍጥነት መገደቢያ በተሰራባቸው አካባቢዎች የአንድም እግረኛ ህይወት አላላፈም። የትራፊክ አደጋና የትራፊክ ደህንነትና ፍሰት ችግሮች ተለይተው በተለይም የእግረኛ መንገድ ማቋረጫዎችና ትምህርት ቤቶች አካባቢ ትኩረት በመስጠት ከበጎ ፈቃደኞች ጋር እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል። ባለፈው ክረምት 350 የበጎ ፈቃደኞች በተሰማሩበት ወቅት ምንም አይነት የትራፊክ አደጋ አለመከሰቱንም አቶ ታመነ ጠቅሰዋል። ከዚህ ልምድ በመነሳት በበጋ 450 በጎ ፈቃደኞች የተሰማሩ ሲሆን ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም