የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ውጤት አላመጣም---የአማራ ክልል ምክር ቤት አበላት

120
ባህርዳር ጥቅምት 24/2011 በአማራ ክልል የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ውጤት እንዳላመጣ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የክልሉ ምክር ቤት አበላት ገለፁ። በክልሉ እየተሰጠ ያለው የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት የባለድርሻ አካላት ቅንጅት የጎደለው በመሆኑ የአርሶ አደሩን እውቀትና ክህሎት ከማሳደግ አንጻር ውጤት እንዳላመጣም አባላቱ ተናግረዋል። የምክር ቤት አባል አቶ ይልማ ወርቁ  እንደገለፁት የተቀናጀ የጎልማሶት ትምህርት የአርሶ አደሩን ሁለንተናዊ እውቀት በማሳደግ ስልጡንና የተማረ አርሶ አደር ለማፍራት አላማ እድርጎ የሚካሄድ ነው። አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ፈጥኖ በመተግበር ምርትና ምርታማነትን እንዲያሳድግ ድርሻ ይኖረዋል ተብሎ የሚካሄድ መርሃ ግብር መሆኑን የገለጹት የምክር ቤቱ አባል "ይሁን እንጂ ፕሮግራሙ ከምዝገባ ባለፈ በተግባር እየተሰራበት አይደለም "ብለዋል። በደባርቅና ደባት ወረዳዎች ተዘዋውረው በአካል በተመለከቷቸው  ትምህርት ቤቶች የመርሃ ግብሩን ውጤታማ አለመሆን እንዳረጋገጡ የሚናገሩት አቶ ይልማ  ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ አንዳለሆነ ጠቁመዋል፡፡ መርሃ ግብሩ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተውና ተናበው ሊሰሩ እንደሚገባ የጠቆሙት የምክር ቤት አባሉ፤ ችግሮች እንዲፈቱም አስፈፃሚውን አካል በመከታተልና በመቆጣጠር የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል። የሰው ሀብትና ቱሪዝም ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በበኩላቸው የተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርት ግንዛቤ ተፈጥሮበት እየተተገበረ አይደለም። ቋሚ ኮሚቴው በ6 ወረዳዎች በሚገኙ 21 ትምህርት ቤቶች ባደረገው ምልክታ በተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርት የሚቀርበው ሪፖርትና በተግባር የሚስተዋለው የማይገናኝ ነው። "በባለቤትነት የሚመሩት የትምህርት ፣ ጤና፣ ግብርና፣ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጉዳዩን የኔ ነው ብለው በባለቤትነት እየሰሩት አይደለም "ያሉት ሰብሳቢዋ በጋራ ተገናኝተው ስራዎችን በመገምገምና በማስተካከል ረገድም ጅምር ስራ እንደሌለ ገልፀዋል። የቋሚ ኮሚቴ አባላት ባደረጉት ምልከታም የተማሪዎች ምዝገባ እንዳልተጠናቀቀ፣ የቅድመ መደበኛ ትምህርትም ከመደበኛው ተማሪ ጋር ተዳብሎ እየተሰጠ መሆኑን ወይዘሮ ፋንቱ አስታውቀዋል። የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፋለ ባለፉት ዓመታት መርሃ ግብሩን ውጤታማ ለማድረግ ከ15 ሺህ በላይ አመቻቾችን የመቅጠር ስራ መከናወኑን አስታውሰዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ጎልማሶችን በመመዝገብ ለማስተማር ጥረት መደረጉን የገለጹት የቢሮው ኃላፊ በዚህ አመትም አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ጎልማሶች እንዲመዘገቡ ተደርገዋል ብለዋል፡፡ የተመዘገበው በቁጥር ደረጃ ከፍተኛ ቢሆንም በባለ ድርሻ አካላት የቅንጅት መጓደልና  በአሰራር ችግር መርሃ ግብሩ ውጤታማ አለመሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በሀገር አቀፍም ሆነ በክልል የመርሃ-ግብሩ የአፈጻጸም ችግር መለየቱን የገለጹት ዶክተር ይልቃል በአዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ የዳሰሳ ጥናት የተካተተ በመሆኑ ችግሩ ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ የአማራ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር፣4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ አዋጆችን በመገምገም ያፀደቀ ሲሆን ማምሻውን የተለያዩ ሹመቶችን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም