ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ፖሊስ የጎላ ሚና አለው---አቶ ለማ መገርሣ

86
አምቦ ጥቅምት 24/2011 የተጀመረው ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረውና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ፖሊስ የጎላ ሚና እንዳለው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሣ ገለጹ፡፡ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ በምዕራብ ሸዋ ዞን ሰንቀሌ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ለ27ኛ ጊዜ  ያሰለጠናቸውን 6ሺህ የፖሊስ አባላት  ዛሬ አስመርቋል፡፡ በምረቃ ስነ ስርዓት ወቅት የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሣ እንዳሉት በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው ፖሊስ ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ "የዛሬዎቹ ተመራቂዎችም ከራሳችሁ በላይ የህዝብን ጥቅም በማስቀደም የተገኘው ሁሉን አቀፍ ለውጥ ዘላቂ እንዲሆን የተጣለባችሁ ህዝባዊና አገራዊ ኃላፊነት ታላቅ ነው" ብለዋል፡፡ ለውጡ እንዳይቀለበስ ፖሊስ አስቀድሞ ሊፈጠር የሚችልን ወንጀል አውቆ መከላከል እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ዳይሬክተር ኮማንደር ጌታቸው ኢታና በበኩላቸው ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኑ የፖሊስ አባላት የሰላም አምባሳደር በመሆን ህዘቡን እንዲያገለግሉ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው ገልጸዋል፡፡ ተመራቂዎችም በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በታማኝነት ማገልገል እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል፡፡ ዛሬ ያስመረቋቸው 6ሺህ የፖሊስ አባላት ባለፉት ሁለት ወራት ፖሊሳዊ ስነ ምግባር፣ ወንጀልን ቀድሞ ስለመከላከል፣ በህገ መንግስት ማስከበርና ተያያዥ ፖሊሳዊ ሙያ በተግባር የተደገፈ ስልጠና መውሰዳቸውን አስታውቀዋል። ከተመራዎቹ መካከል ኮንስታብል ወይኒቱ ታደሠ በስልጠና ወቅት ያገኘችውን ክህሎት በመጠቀም ሁሉንም ዜጋ በእኩልነት ለማገልገል መዘጋጀትዋን ተናግራለች። "ሰላም በማስከበርና ወንጀልን ቀድሞ በመከላከል ሂደት ውስጥ የህበረተሰቡ አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ህዝቡም ከፖሊስ ጎን መቆም ይኖርበታል" ያለው ደግሞ ሌላው ተመራቂ ኮንስታብል ፈይሣ ከተማ ነው፡፡ በምረቃው ስነስርዓት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንትን ጨምሮ፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም