የጋና እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት በሙስና ተጠርጥረው ታሰሩ

86
አዲስ አበባ ግንቦት 15/2010 የጋና እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ክዌሲ ንያንታኪ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ታሰሩ። የአገሪቱ ታዊቂ የምርመራ ጋዜጠኛ አናስ አርሜያው አናስ "ቁጥር 12" በሚል ርዕስ በጋና እግር ኳስ ውስጥ ስላለው ሙስና የሰራው ዘጋቢ ፊልም ለፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት መታሰር ምክንያት መሆኑን ጋና ዌብ በድረ-ገጹ አስፍሯል። የጋና ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ ዘጋቢ ፊልሙን ከተከታተሉ በኋላ የጋና የፖሊስ አገልግሎት የወንጀለኛ ምርምራ ክፍል የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንቱን በቁጥጥር ስር እንዲያውል በሰጡት ትዕዛዝ ክዌሲ ንያንታኪ ትናንት ሊያዙ ችለዋል። ዘጋቢ ፊልሙ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከሌሎች አካላት ጋር በመደራደር ገንዘብ ለማግኘት የሚያደርጉትን ተግባር የሚያሳይ ነው። ፊልሙ ክዌሲ ንያንታኪ ሞሮኮ ውስጥ ካሉ የንግድ ሰዎች ጋር የጋና ብሔራዊ ቡድንን ስፖንሰር ማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ውይይት ሲያደርጉና ሞሮኳዊያኑ የንግድ ሰዎች በአገሪቷ የተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮች መዋዕለ-ነዋይ ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ሲገልጹ ያሳያል። የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ከሞሮኮ የንግድ ሰዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ ጉቦ የሚሰጡ ከሆነ ከጋና ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት ጋር በቀላሉ እንደሚያገናኛቸው መናገሩ ነው የተገለጸው። "ጋና ንግድን ለማከናወን የተመቸች አገር ናት፤ ለፕሬዝዳንቱ አምስት ሚሊዮን ዶላር ለምክትል ፕሬዝዳንቱ ሶስት ሚሊዮን ዶላር ከሰጣችሁ በቂ ነው። እኔ ፕሬዝዳንቱን በየቀኑ አገኘዋለሁ" በማለት ለሞሮኮ የንግድ ሰዎች እንገለጹላቸው ተነግሯል። በዘጋቢ ፊልሙ ላይ ከስልጣን የተባረሩት የጋና የስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ሚስተር ቢየስ ኢናም ሀዚዴና ረዳታቸው ሚስተር አሴንሶ ቦካዬ የሞሮኮ የንግድ ሰዎች ከፕሬዝዳንቱ ጋር እንዲነጋገሩ የሚያመቻቹ ተጨማሪ አገናኞች መሆናቸውንም የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ተናግረዋል። ከፕሬዝዳንቱ ጋር ለማድረግ የታሰበው ውይይት ከተሳካ የሞሮኮ የንግድ ሰዎች ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አንድ ሚሊዮን ዶላር እንደሚሰጡት ሲነግሩትም የዘጋቢው ፊልም እንደሚያሳይ የጋና ዌብ ዘገባ ያትታል። የሞሮኮ የንግድ ሰዎች ክዌሲ ንያንታኪ መጥቶ ስላናገራቸው 65 ሺህ ዶላር እንደሰጡት ዘገባው ያመላክታል። በተጨማሪም በዘጋቢ ፊልሙ ላይ የጋና እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተወሰኑ አባላት በጋና የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከሚገኙ ሴት ተማሪዎች ጋር በግል ጀት ሲዝናኑ እንደሚያሳይ ተገልጿል። የምርመራ ጋዜጠኛ አናስ አርሜያው አናስ ዘጋቢ ፊልሙን ለመስራት ሁለት ዓመት እንደፈጀበትም ታውቋል። የጋና እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ክዌሲ ንያንታኪ ስልጣናቸውን በመጠቀም ያልተገባ ጥቅም ማግኘትና ሰዎችን በማታለል ገንዘብ በመቀበል በሚል ክስ እንደሚቀርብባቸው የተገለጸ ሲሆን ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ 25 ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ተገልጿል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም