ከምክንያታዊነት የራቀ አስተሳሰብ የት ያደርሰናል?

216
ዳግም መርሻ/ኢዜአ/ ሰላም ለእናንተ…….. ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ሰሞኑን በአንድ ካፍቴሪያ በረንዳ ላይ አረፍ  ብዩ እየተዝናናሁ በነበርኩበት ሰአት አጠገቤ የነበሩ በእድሜ ጠና ያሉ ሁለት ግለሰቦች በአሁኑ ወቅት በሀገራችን አንዳንድ አካበቢዎች የሚታዩ ስሜታዊ ድርጊቶችን አስመልክቶ ሲያደርጉ የነበረው የጋለ የሀሳብ ልውውጥ ነው። ግለሰቦቹ በፊት እነርሱ ባለፉባቸው ጊዜያት ህብረተሰቡን ደንብና ስርአት እንዲይዝ የማድረግ አቅም የነበራቸውን ባህላዊ ልጓሞች(እሴቶች) አሁን መሬት ላይ ካለው ሁኔታ ጋር እያነጻጸሩ በቁጭትና በመቆርቆር ስሜት ሲናገሩ ስሰማ  በእርግጥም እነዚህ ዘመን ተሻጋሪ እሴቶቻችን አሁን ባለንበት ወቅት እየታዩ ላሉት ችግሮች ያላቸው ፋይዳ ቀላል የሚባል አለመሆኑ ስለተሰማኝ በዚህ ጉዳይ ላይ ገና ብዙ መባልና መወትወት እንዳለበት ተረዳሁ። እናም ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ ተነሳሳሁ። ለምክንያታዊነት ሰፊና የተለያየ ትርጉም መስጠት ቢቻልም ብዙዎችን የሚያስማማና የሚያግባባ ትርጓሜው፣ የሰው ልጅ እውነትን ፈልጎ የሚያገኝበት የተፈጥሮ ችሎታ መሆኑ ነው። በዚህ መሰረት ቃሉ አንድን ሀሳብ ወይም የተወሰነ ጉዳይ መፈተሸ፣ መመርመር፣ መመዘን፣ ማውጣት ማውረድ… በመጨረሻም እውነታው ላይ ከመድረስ ጋር ይቆራኛል። እናም ምክንያታዊነት ከማሰብና ማስረጃንና መረጃን መሰረት አድርጎ ሀሳብን ከመዳሰስ፣ ከመፈተሸ፣ ከመመርመር፣ ከመሞገት፣ ከማውጣትና ማውረድ… ጋር በእጅጉ የተያያዘ ነው። ምክንያታዊነት ከእሴትና ሞራላዊ ጉዳዮች፣ ለእውነትና ለፍትህ ወግኖ ከመቆምና ከመቆርቆር ፣ ከመቻቻልና ከመከባበር፣ ሰውን በሰውነቱ ከመመዘንና ዋጋ ከመስጠት ጋር ይቆራኛል። በአንጻሩ ዘርን፣ ቋንቋን፣ ሀይማኖትን፣ ጾታን…ወዘተ መሰረት አደርጎ በሰዎች መካከል ልዩነት መፍጠር፣ መጠቃቀም ወይም በእነዚህ ልዩነቶች ላይ በመመርኮዝ መጠቃቃት ምክንያታዊነትንና አርቆ አሳቢነትን አያመለክትም። ለሰው ልጆች በተፈጥሮ ከተቸራቸው የማሰብ ልእልናንም ይጻረራል። ምክንያታዊ ስንሆን ግጭት፣ ንትርክ፣ በጭፍን መጠላላት፣ ጠመንጃ ማንሳትና መገዳደል፣ መጎዳዳት… አያስፈልገንም። የሚያስፈልገን የሀሳብ ልእልናና የአስተሳሰብ የበላይነት ነው። ይህ ደግሞ እውን የሚሆነው ጤናማ በሆነ ውይይትና በመደማመጥ ላይ በተመሰረተ ንግግር ነው። ቀደም ብዬ እንዳልኩት ምክንያታዊነት ሰውን በሰውነቱ፣ በአስተሳሰቡና በማህበራዊና ፖለቲካዊ የህይወት እንቅስቃሴ ውስጥ በሚያበረክተው አስተዋጽኦ የሚመዝን እንጂ በደም፣ በጎጠኝነት፣ በቡድንተኝነት ወይም በመጠቃቀም ላይ የተመሰረተ የእከክልኝ ልከክልህ ግንኙነት አይደለም። ያለምክንያታዊነት፣ ያለሚዛናዊ ሀሳብና ያለ መርህ በሚመራ ግንኙነት ውስጥ አይሎና ገዝፎ የሚንጸባረቀው ስሜታዊነት እንጂ ምክንያታዊነት አይደለም። በርግጥ የሰው ልጅ ሙሉ ለሙሉ ከስሜት ነጻ ነው ወይም ደግሞ ስሜት በጭራሽ አያስፈልግም ማለት እንደማይቻል አንባቢዎቼ እንዲረዱልኝ እፈልጋለሁ። ችግር የሚሆነው ስሜታዊነት ውሉን ስቶ መጎደዳት፣ መቃቃር፣ መከፋፈልና ጥላቻን ሲያሰከትል ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው ነገር ከምክንያታዊነት ስንርቅ ስሜታችን ለጅምላ ፍረጃ ቅርብ መሆኑን ነው፡፡ አንዱ ሌላውን በጅምላ ይፈርጃል፡፡ ብዙዎቻችን በጭፍን ድምዳሜ እንዋጣለን፡፡ አንድን ነገር ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ መርምረን፣ በምክንያት ተንትነን እንዲሁም መረጃና ማስረጃ አቅርበን እውነታው ላይ መድረስ ሲገባን እንደመሰለን እንናገራለን ብሎም እንተነትናለን። «አትግደል»፣ «አትዝረፍ»..የሚለውን  የህሊና ደንብ እንጥሳለን። አብሮና ተሳሰቦ መኖርንም ዋጋ እናሰጣለን። ባስ ሲልም ገጀራ እየነቀነቅን የሚመስለንን ፍትህ አንሰጣለን፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ሚዛናዊ አስተሳሰብና ሰብአዊነት ተሸርሽሮ ጠባብነት፣ ዘረኝነትና ግዴለሽነት ሲናኝ ነው። እንደዚህ ከሆነ ዘንዳ የሰው ልጅ አእምሮ (ጭንቅላት) የጸጉር ማብቀያ ብቻ ሳይሆን ማሰቢያና የምክንያታዊ አስተሳሰብ መፍለቂያ መሆኑን መረዳት እንችላለን። ከዚህ በተቃራኒ አእምሯችን ከምክንያታዊ አስተሳሰብ ይልቅ አሉታዊ ስሜታዊነትን ይዞ የሚነዳን ከሆነ የምናደርገው ድርጊት ጎጂነቱ የሚያመዝን ይሆናል። ጉዳቱ ዜጎችንም ሀገርንም ዋጋ ያስከፍላል። ስለሆነም ምክንያታዊነት እንዴት? ለምን?  መቼ?  የት?  ምን?  የመሳሰሉትን መሰረታዊና አመክንዮን የተከተሉ ወሳኝ ጥያቄዎችን በማንሳት እውነትን ከሀሰት አብጠርጥሮ ማጥራትን ይጠይቃል፡፡ በዚህ መልኩ ጠያቂና ሞጋች ትውልድ ሲኖር አገርና ዜጎች ከአሉቧልታና ከሀሰተኛ ወሬ ይድናሉ። ከዚህም በተጨማሪ ማህበረሰቡ እራሱን የለተለያዩ ጉዳቶች ሰለባ እንዳይሆን መጠበቅ ይችላል። ከዚህ ሁኔታ በመነሳት ባሁኑ ወቅት በግላጭ የሚታየውን የሀገራችንን ሁኔታ ስንቃኝ ከምክንያታዊነት ይልቅ ስሜታዊነት በርትቶ የሚታይበት ጊዜ ላይ ነን ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታይና የሚዳሰስ ችግር መሆኑ አሌ አይባልም። ለዚህ ማሳያዎችን በተለያዩ መገለጫዎች በማስደገፍ ማቅረብ ይቻላል። ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የቆየ አብሮ ተሳስቦና ተዛዝኖ በጋራ የመኖር አኩሪ ባህል ያለን ህዝቦች አንደሆንን ይታወቃል። በሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫ ዘልቆ ያልተጋባ፣ ያልተዋለደና ያልጠቀየጠ ህዝብ የለም። ይህ የሚያሳየው በደም መተሳሰራችንን ነው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ ሁሉም የኛ ነው ቢባል ስህተት ነው ብዬ አላስብም። ይሁንና አሁን መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ስናይ ይህ የቆየ እሴትና ኢትዮጵያዊ ማንነት ተዘንግቶና ተሸርሽሮ “እኛና እነርሱ” የሚል ግንብ ተገንብቶ የእኛ ብሄር ተነካ፣ እንዲህ ሆንን፣ እኛ እንደዚህ ነን…ማለት አብዝተናል። የጠባብነት ህልምም ተጠናውቶናል። ይህን በየማህበራዊ ሚዲያው፣ በየጎዳናው፣ በተለያዩ መድረኮችና በየአካባቢው አሰተውለናል። የዚህ ሌላው መገለጫ “ሁሉም የኛ ነው፣ እናንተ መጤ ናችሁ...” ወይም  “አንድ አይነት ካልሆንን አንድ አይደለንም” የሚለው አስተሳሰብ ነው። መነሻና ምንጩም በምክንያታዊነት ላይ ያልተመሰረተ ጭፍን ጥላቻ ነው። ይህ ደግሞ ስሜትን አግሎና አንሮ  እዚህም እዚያም አሳፋሪ በሆነ መልኩ ህይወት ሲጠፋና ዘግናኛ ጥፋት እንዲደርስ አድርጓል። እያደረገም ይገኛል። ይህ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ካዳበሩት አብሮ የመኖር ባህልና የማህበራዊ ህይወት መስተጋብር በእጅጉ ተጻራሪ ነገር ነው። ለመሆኑ በፊት በህብረተሰቡ ውስጥ በስፋት የነበረው ምከንያታዊነት፣ አስተዋይነት የተላበሰው  እሴት ለምን ተዳከመ? ለመዳከሙ ሀላፊነት የሚወስደው ማን ነው? አሮጊውን አፍርሶ አዲስ መገንባት የትስ ለመድረስና ምን ተአምር ለመፍጠር ነው? አሁን እንደሚታየው ከመጎዳዳት በስተቀር ምን ፋይዳ ያመጣል? እነዚህ ሁሉ ብዙ ንግግርና ውይይት ማድረግ የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች ይመስሉኛል። ለነገሩ ይህ ከምክንያታዊነት ርቆ በስሜት የመነዳት ሁኔታ በሌሎችም አካባቢዎች ይስተዋላል። በስፖርቱ ዘርፍ ያለውን ሁኔታ እንኳን ብናይ ስፖርተኞቻችን በሩጫ ወይም በእግር ኳስ ሲያሸንፉም  ሆነ ሲሸነፉ ብዙዎቹ ስሜታቸውን በልኩ መቆጣጠር ተስኗቸው ሲረብሹና ሌላውን ሲያውኩ ማየት የተለመደ ነገር ነው። በስቴዲዮሞችና በሰላማዊ ሰልፎች ውስጥም የሚስተዋለው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም። አዳዲስ የመንግስት ሀላፊዎች ሲሾሙ ተሿሚዎችን በእውቀታቸው፣ በልምዳቸውና በችሎታቸው ከመመዘን ይልቅ ድጋፍ የምንሰጠውም ሆነ የምንቃወመው ብዙ ጊዜ በብሄር ማንነታቸው ላይ ተመስርተን ነው። በእኛ ሀገር ማን አለ እንጂ ምን አለ ለሚለው ጉዳይ ብዙ ትኩረት አንሰጥም። አንድን ግለሰብ ወይም ፓርቲ ለምን ደገፍከው ተብሎ ጥያቄ ሲቀርብ በብዙዎች የሚሰጠው ምላሽ ምክንያትነቱ ውሀ አያነሳም። እንዲያውም ብዙ ግለሰቦች ስለሚደግፉት ፓርቲ አላማና ፖሊሲ በቂ ግንዛቤ የላቸውም። ከጥቂቶች በስተቀር ስለእነዚህ ጉዳዮች አንብበውም ይሁን ጠይቀው የማያውቁም ብዙ ናቸው። ይህ «ተምረናል » የሚባሉትንም ይጨምራል። ስለሆነም እነዚህን መሰል ጥራዝ ነጠቅ አስተሳሰቦች በምክንያታዊ የሃሳብ የበላይነት እስካልተሸነፉና እንደህዝብ ነገሮችን ሰከን ብለን የመመርመር ባህል እስካላዳበርን ድረስ በተሳሳቱ መንገዶች ደግመን ደጋግመን ጥፋት ውስጥ ስላለመመለሳችንና ችግር ውስጥ ስላለመክረማችን ምንም ዋስትና የለም። ምንም እንኳን ከላይ የተጠቀሰው በስሜት የመንጎድ ችግር ጎልቶ የሚታየው በቀለም ባልገፉት ግለሰቦች ላይ ነው ተብሎ ቢታመንም በዘመናዊ ዲሞክራሲ ባህልና አሰራር ዳብረዋል በሚባሉት ምእራባውያን ሀገራት ውስጥ የቀለም ትምህርት ቀስመውና ለረጅም አመታት ኑሮዋቸውን አዛው አድርገው የመጡ ግለሰቦችም ጭምር የዚህ አይነቱ ችግር ሰለባ ናቸው ማለት ይቻላል። እንደሚታወቀው ምሁር ማለት በተለምዶ ዩንቨርስቲ ዘልቆ ዲግሪና ዲፕሎማ የያዘ ወይም ብዙ ያነበበና በተለያዩ መስኮች ጥናትና ምርምርን ያደረገ ነው ማለት ብቻ አይደለም። ምሁርነት ከዚህም ከፍ ያለ ሀሳብ ነው። ምሁርነት በዋናነት ከስሜት ይልቅ በምክንያታዊነት፣ ከአፈሙዝና ከጭፍን ጥላቻ ይልቅ የሀሳብ ልእልና፣ ከአድርባይነት ይልቅ በመርህ እና በአመክንዮ መመራት፣ ከውዥንብር ይልቅ አቅጣጫ ማሳየትን፣ ከፕሮፓጋንዳ ይልቅ እውነትን በግብር ከመግልጽ የአኗኗር ዘይቤ ጋር ጋር የተያያዘ ነው። ሆኖም  ባሁኑ ወቅት በተግባር እየሆነ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት በምክንያታዊነትና ከላይ ከተጠቀሱት የምሁርነት መገለጫዎች አንጻር በህዝብ ውስጥ በስፋት የሚታወቁ ጥቂት ግለሰቦች ቢኖሩም በዚያው ልክ ደግሞ ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል ባልተለየ ሁኔታ ከምክንያታዊነት ርቀው በስሜት የሚነዱ፣ ልዩነት ተፈጥሯዊ መሆኑን በመዘንጋት ሌሎች ወገኖችን የሚፈርጁና የሚያብጠለጥሉ፣ ታሪክንና እውነትን አጣመው የሚያቀርቡ፣ ለርካሽ የፖለቲካ ፍጆታ ሲሉ ሌሎችን የሚያጠለሹ (ስም የሚያጠፉ)፣ አንዱን ብሄረሰብ ከሌላው ብሄረሰብ ጋር ግጭት እንዲፈጥር የሚቀሰቅሱና የሀሰት አሉቧልታ የሚነዙ «ምሁራን» ተብዬዎች ቁጥራቸው ጥቂት የሚባል አይደለም። በዚህም በተማረውና ባልተማረው የህብረተሰብ ክፍል መካከል ያለው ልዩነት እየደበዘዘ ሁሉም በአንድ ቦይ ውስጥ በስሜት ሲፈስ ይታያል። ሌላው ከዚህ ጋር በተያያዘ ትልቅ ችግር የሚስተዋለው በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ነው። ብዙዎቹ ፖለቲካ ፓርቲዎች አላማቸውንና ርእዮተ አለማቸውን ለህዝቡ በማሳወቅና በማስረዳት ደጋፊዎችን ከማፍራት ይልቅ አባሎቻቸውን በስሜት ቆስቋሽ ጉዳዮች በመጥመድ ደጋፊን በማብዛት ላይ ስለሚያተኩሩ የህዝቡን ንቃተ ህሊና ከፍ በሚያደርጉ ሃሳቦች፣ በህዝቡ (በሀገሪቱ)ችግሮችና በሌሎች አጀንዳዎች ዙሪያ በሰከነ መንገድ የሚካሄዱ ንግግሮችና ውይይቶች እጅግ አነስተኛ ናቸው። ሀሳብና ምክንያታዊነትን የሚያበረታታ ሁኔታ በሌለበት ስፍራ ደግሞ ቦታውን የሚይዘው ግጭት፣ ንትርክ፣ አሉቧልታና ውዝግብ ነው። ምክንያታዊ ብንሆን አሁን ላይ እንደሚታዩት ንትርክ፣ መጠላላትና የእርስ በርስ የገመድ ጉተታን ባላስተዋልን ነበር። ከዚህ ርእሰ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ሀሳቡን ያካፈለኝ አንድ የስራ በልደረባዬ እንደሚናገረው እርሱ ተወልዶ ባደገበት በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ መስመሩን እንዳያልፍ ወይም እንዳይፈጽመው የሚጠነቀቅለት በኦሮሚኛ «ጩቡ» የሚባል ነገር አለ። ከገዳ ሥርዓት በሚመዘዝ በዚህ የማህበረሰብ እሴት መሠረት መዋሸት፣ እውነትን መደበቅ፣ ሰውን መበደል፣ ግፍ መስራት፣ ተመጣጣኝ ያልሆነ ጉልበት መጠቀም፣ ነፍስ ማጥፋት፣ ሰዎች በአግባቡ እንዲጠቀሙ በፈጣሪ የተሰጠን ሃብት ማውደም ...  “ጩቡ” ነው። የአማርኛ ኣቻ ትርጉሙ ሀጢያት ሲሆን፤ ይህም ዘር ቆጥሮ እስከ ልጅ-ልጅ ተከታትሎ በመምጣት ጥፋት ያስከትላል ተብሎ ስለሚታመን በማህበረሰቡ ትልቅ ግምት ይሰጠዋል። በዚህ ባህላዊ እሴት ምክንያት ሁለት ሰዎች ተጣልተው ቢደባደቡና አንዱ ቢወድቅ የወደቀውን መምታት እንደማይቻል፤ ቅጣቶች ልክ የተበጀላቸውና በሰብአዊነት ስሜት ይፈጸም እንደነበር አጫውቶኛል። ይህ እሴት አሁንም ቢሆን በብዙ ቦታዎች ማህበረሰቡ ጠብቆት ያቆየው እንደሆነና ይህ የሚጠፋ ከሆነ ግን እንደማህበረሰብ አብሮ ለመቆም ልንቸገር እንደምንችል ስጋቱን ገልጾልኛል። ምክንያታዊ ሀሳብ በማህበረሰቡ ውስጥ እየተሸራረፈ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ የግል እይታቸውን ያካፈሉኝ ሌላው የቅርስ ጥበቃና ጥናት ባለሙያውና ተመራማሪው አቶ ሀይለመለኮት አግዘው በበኩላቸው በተለያየ የሀገራችን ማህበረሰቦች ውስጥ ህብረተሰቡ እንደፈለገ እንዳይፈነጭ፣ ያጠፋ ለተበደለ ካሳ የሚክስበት፣ እርስ በርስ ተሳስቦና ተከባብሮ በጋራ ለመኖር የሚያስችሉ ባሀላዊ የአሰተደደር ዘይቤዎች በተለያዩ ብሄረሰቦች ዘንድ እንደሚገኙ በማንሳት እነዚህ እሴቶች ምክንያታዊ አስተሰሰብን ለማጠናከር ያላቸው ፋይዳ ትልቅ መሆኑን ይናገራሉ። ሌላው ቀርቶ በፊት በስፋት የነበሩትና አሁን አሁን እየቀሩ የመጡት የቄስና የአብነት ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የሀይማኖት ተቋማት ከቤተሰብ ቀጥሎ ትውልዱ ስርአት ይዞና በስርአቱ ተቀርጾ እንዲወጣ ከማድረግ አኳያ የነበራቸው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ እንዳልነበር ያብራራሉ። ይሁንና እነዚህ ተቋማት ሲዳከሙ የአብዘኛው ህብረተሰብ  የሞራል ልእልና ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ መምጣቱንና ኢትዮጵያዊነትም አደጋ ላይ መውደቁን አክለው ይገልጸሉ። ለዚህ ደግሞ ከመንግስት ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የሀይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የመገናኛ ብዙሀን፣ ወላጆች ..ሀላፊነት የሚወስዱ አካላት መሆናቸውን ያስረዳሉ። ከላይ የተነሱት ሀሰቦች የሚያስገነዝቡት ነገር ቢኖር አሁን ያለው አብዛኛው ማህበረሰብ የራሱን እሴቶችና ባህል ወደጎን ብሎ ከኛ ሁኔታና ባህል ጋር የማይሄዱና የማይጣጣሙ አስተሳሰቦች፣ እሴቶችና ባህሎችን በመኮረጅ ላይ ስለተጠመደ ችግር ውስጥ እየገባ መሆኑን ነው። ከዚህ ጋር የሚያያዘው ሌላው ችግር ያሉንን እሴቶች ላሁኑ ትውልድ በማሸጋገርና በማሳደግ ረገድ ብዙና በቂ ስራ እንዳልተሰራ ነው። ይህ ማለት ግን አሁን ያለው ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው ብዬ አላምንም። አሁን አንኳን በቅርቡ የጋሞ አባቶች ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴን በመጠቀም በስሜት ተነሳስተው ጥፋት ሊያደርሱ የነበሩ ወጣቶችን ያስቆሙበት መንገድ ለብዙዎች ተስፋን የጫረና ሌሎች አካባቢዎችም ልክ እንደጋሞ አባቶች ባህላዊ እሴቶቻቸውን ለሚታዩ ችግሮች እንደመፍትሄ መጠቀም እንዳለባቸው ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ ነው። እንደ አጠቃላይ ግን ከላይ ለተጠቀሱት ችግሮች መፍትሄ ካስፈለገ እንደ ህዝብ እውነት እውነቱን መነጋገር አለብን ብዬ አስባለሁ። በእኔ እምነት የሀገራችን የአኗኗር ባህል፣ ስርአተ ትምህርቱና የፖለቲካ ግንኙነትና ልማዳችን ለዲሞክራሲው እድገት እንድንጠይቅና እንድንሞግት የሚገፋፋና የሚያበረታታ አይደለም። ከዚህ በተጨማሪም ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው መንግስት፣ ምሁራን፣ የፖለቲካ ሊሂቃን፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ መገናኛ ብዙሃን፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ወዘተ. በሀሳብ ልእልና ዙሪያ በበቂ ሁኔታ እየሰሩ ነው ማለት አይቻልም፡፡በሌላ በኩል ሀሳባዊነትና የምክንያታዊ አስተሳሰብ ዝም ብሎ እንደችግኝ የሚበቅል ነገር ሳይሆን ብዙ ስራ ተሰርቶ የሚመጣ ነገር ነው። ስለሆነም ምክንያታዊነትንና የሀሳብ ልእልናን በሀገር ደረጃ ለማበልጸግ የእነዚህ አካላት ተሳትፎና አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ለሀገር እድገት፣ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትም ወሳኝነት አለው። እነዚህ አካላት ዜጎች ልዩነቶችን በምክክር፣ በውይይትና በንግግር እንዴት መፍታት እንደሚቻል እራሳቸው ምሳሌ ሆነው ለህብረተሰቡ ሊያሳዩት ይገባል። ባሁኑ ወቅት በሀገራችን የሚታየው ችግር አንዱ  ምክንያት የምክንያታዊነትና የመቻቻል ባህል መመናመን ነው። ስለሆነም በዚህ በኩል ያለውን ችግር ለመለወጥና የነቃ፣ በደንብ የሚያስብ፣ የሚጠይቅና የሚመራመር ህብረተሰብ ለመፍጠር የእነዚህ አካላት አስተዋጽኦና ርብርብ ቁልፍ ነገር ነው። በተለይ ደግሞ በልምድ ለተፈተኑ፣ ለተከበሩና  ለበሰሉ ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች መድረክ በመክፈት ሀሳባቸውን ለህብረተሰቡ እንዲያካፍሉና አቅጣጫ እንዲያመላክቱ ማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው። ሁላችንም እንደምናውቀው ኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ ብዙ  ችግሮች ያሉባት ሀገር ናት። በአሁኑ ጊዜ  በሀገሪቱ ብዙ የፖለቲካና የልማት ጥያቄዎች አሉ። በአንጻሩ ደግሞ አለም መጥቃ በብዙ ርቀት ጥላን ሄዳለች። ከእነዚህ ሁኔታዎች አኳያ ባሉን ችግሮች ላይ ሌላ ተጨማሪ ችግር ማብዛት አለብን ብዬ አላስብም። ማድረግ ያለብን ነገር ቢኖር እንደሰለጠነ ሰው መወያየትና መነጋገር ነው። አንዳችን ለአንዳችን ወዳጅ እንጂ ጠላት አይደለንም። ስለሆነም መፍትሄው ባሉት ችግሮችና ጥያቄዎቻችን ላይ በመወያየት ወደ እውነቱና ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ወደሚያጠናክረው መንገድ ተያይዘን መጓዝ ነው። ከምክንያታዊነት በራቀ ሁኔታ ጫፍና ጫፍ ይዘን መሄድ እንደትልቅ ሀገርና ህዝብ ለኛ ምንም ጥቅም የለውም። ስለሆነም ለችግሮቻችን መፍትሄ ሰጪዎቹ እኛው እንደሆንን አምነን ለዚሁ በሙሉ ልብ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል። እንደዚያ ከሆነ ችግሮቻችንን መፍታት እንችላለን። አለበለዚያ ግን በስሜታዊነት ተሸንፈን ተያይዘን መውጣት ወደማንችለው ማጥ ውስጥ የመግባታችን እድል የሰፋ ነው ባይ ነኝ። ቸር እንሰንብት!  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም