ለጋምቤላ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የድርሻችንን እንሰራለን...የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች

58
ጋምቤላ ጥቅምት 24/2011 በጋምቤላ ከተማ ተፈጥሮ የነበረውን የሰላም ችግር ወደ ነበረበት ለመመለስ በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የከተማው ነዋሪዎች ገለጹ። ነዋሪዎቹ ከከተማው አስተዳድር አመራሮችና የጸጥታ አካላት ጋር በከተማው በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትላንት ተወያይተዋል። በመድረኩ ላይ ከተገኙት ተሳታፊዎች መካከል አቶ አቡላ ኡቦንግ በሰጡት አስተያየት ህዝቡ ልዩነቶችንና ያለፉ ችግሮችን በመተው ለአካባቢያቸው ሰላም ከሌሎች ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጅት አድርገዋል። ክልሉ በተደጋጋሚ በግጭት መነሳት እንደሌለበት ጠቁመው በተለይም ወጣቱን በመምከር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚያግዙም ተናግረዋል። “በመካከላቸው ያለውን ጥላቻ በማስወገድ ለከተማው ብሎም ለክልሉ ሰላምና ልማት በጋራ መስራት እንደሚገባ” የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ኛሉዋል ዴንግ ናቸው። ''ኑዌርና አኝዋሃ መካከለቸው የሚፈጠሩ ግጭቶችን በማስወገድ አንድነታቸውን በማጠናከር ለክልሉ እድገት መስራት አለባቸው ''ሲሉም ተናግረዋል። ሌላው ተሳታፊ አቶ ኦቦንግ ኦጃቶ በሰጡት አስተያየት በመካከላቸው ችግር የሚፈጥሩ አካላትን አጋልጦ ለህግ በማቅረብ ሰላማቸውን ለማረጋገጥ መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል። በከተማው ቀደም ሲል ተፈጥሮ ከነበረው የሰላም ችግር ጋር ተያይዞ በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ትምህርታቸውን በተሟላ ሁኔታ እየተከታተሉ አለመሆናቸውን ገልጸዋል። ስለሆነም በተለይም ወጣቱን መክሮ በማሳመን ከተማዋን ወደ ቀድሞ ሰላሟ ለመመለስ የድርሻቸውን እንደሚሰሩም ተናግረዋል። የጋምቤላ ከተማ ከንቲባ አቶ ቺቢ ቺቢ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ችግር ፈጣሪዎችን ለህግ አጋልጦ በመሰጠት ረገድ ከህብረተሰቡ የላቀ ድርሻ ይጠበቃል። የከተማ አስተዳድሩ በአሁኑ ወቅት በተለይም በከተማው ተፈጥሮ የነበረውን የሰላም ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጀት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በአግባቡ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ አይደለም በሚል ለተነሳው ሃሳብም “በትምህርት ቤቶቹ ግብር ኃይል በማቋቋም ተማሪዎቹ  ያለ ስጋት  ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ይደረጋል” ብለዋል። ክልሉን የሚመራው የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አዲሱ አመራር የክልሉን ሰላም በማስጠበቅ ልማቱን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አዲስ አበባ ላይ ባደረገው የማዕከላዊ ኮሚቴ ጉባኤው ቃል መግባቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም