ጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም በተቀናጀ መንገድ መከላከል ይገባል

1328

አዲስ አበባ ጥቅምት 23/2011 በዓለም የብዝሃ ህይወት ቅርስነት መዝገብ በሰፈረው ጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም በተቀናጀ መንገድ መከላከል እንደሚገባ የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የአካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲትዩት በበኩሉ እምቦጭ አረምን በስነ ሕይወታዊ ዘዴ ለማጥፋት ከአራት ዓመታት በፊት አንስቶ ምርምር አያደረገ መሆኑን ገልጿል።

ኢትዮጵያ ውሰጥ በዩኔስኮ የዓለም ብዝሃ ህይወት ወይም ባዮስፌርነት ከተመዘገቡ አምስት የመካነ ሕይወት አካባቢዎች አንዱ ጣና ሃይቅ ነው።

ባዮስፌሩን ለማስተዳደር ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት የማይክሮ ብዝሃ ህይወት ዳይሬክተር ዶክተር ገነነ ተፈራ ለኢዜአ እንደተናገሩት እምቦጭን ለማጥፋት መካኒካል፣ ባዮሎጂካል፣ ኬሚካል ወይም ሌላ ዘዴ ብቻቸውን አማራጭ አይሆንም።

ለዚህም ነው የሌሎች አገሮችን ልምድ በመውሰድ ሳይንሳዊ የሆነ የተቀናጀ የመከላከያ አሰራር መተግበር ያስፈልጋል የሚሉት።

አረሙ በቀላሉ ሊባዛ የሚችል በመሆኑ አደጋው ለጣና ብቻ ሊሆን እንደማይችል ያብራሩት ዶክተር ገነነ ባለድርሻ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በቅርብ ጊዜ ባዮ ስፌሩን መረከቡን የሚገልጹት ዶክተር ገነነ፣ የአረሙን ደረጃ ማሳወቅ፣ ዐውደ ጥናትና ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች ማከናወኑን አንስተው፤ አረሙን ማስወገድ ግን ለኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ብቻ የሚተው አይደለም ብለዋል።

በኢትዮጵያ የአካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲትዩት በበኩሉ በእምቦጭ አረም ላይ ምርምር እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

በእምቦጭ ላይ የሚደረገውን የምርምር ቡድን የሚመሩት አቶ አዱኛ አድማስ እንዳሉት ከአራት ዓመታት በፊት ጀምሮ በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን አረም በሚያጠፋ የኬሚካልና ስነ ሕይወታዊ ዘዴዎችን እየሞከሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ቅጠሉን ሊያጠፉ የሚችሉና ከአካባቢው ላይ የጎንዮሽ ጉዳት የሌላቸው ኬሚካሎች በምርመር መገኘታቸውን ገልጸው፤ ነገር ግን ከጣና ኃይቅ ስፋትና ከኬሚካል የገንዘብ አቅም አንጻር ትልቅ ችግር ሆኗል ብለዋል።

በሌላ በኩል በስነ ሕይወታዊ ዘዴ እምቦጭን ለማጥፋት ከአራት ዓመታት በፊት የተጀመረ ጥናት መቀጠሉን ገልጸው፤ እምቦጩን ሊያጠፉ የሚችሉ ፈንገሶች በጣና ዳር የምርምር ቦታ ላይ ሙከራ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ስነ ሕይወታዊ ዘዴ ሰፊና ጥንቃቄ የተሞላበት ጥናት አንደሚፈልግ ገልጸው፤ ጥናቱን በአንድ ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ማቀዳቸውን አብራርተዋል።

እምቦጭ በሃይቁ ላይ የሚደረገውን ትራንስፖረት ከማስተጓጎልና በአሳ አስጋሪ ወጣቶች ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተዕጽኖ ከማሳደር አልፎ፣ ለቢልሃረዝያ በሽታ ስጋት አንዳለውም በሌሎች አገር ጥናቶች ተረጋግጧል ብለዋል።

በዚህም በሃይቁ ላይ የተከሰተውን አረም ለማጥፋት እንደ ቪክቶሪያ አይነት ሃይቆች ላይ የተወሰደውን የተቀናጀ የመካለከል አመራር መከተል አንደሚገባ ተናግረዋል።