የብዝሃ ሕይወት ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም የጥበበ ሕይወት (ባዮ ቴክኖሎጂ) ምርምርን ማጠናከር ይገባል-ተመራማሪዎች

1598

አዲስ አበባ ጥቅምት 23/2011 ኢትዮጵያ የብዝሃ ሕይወት ሀብቷን በአግባቡ ለመጠቀም የጥበበ ሕይወት (ባዮ ቴክኖሎጂ) ምርምርን ማጠናከር እንደሚገባ የዘርፉ ተመራማሪዎች ተናገሩ።

በጥበበ ህይወት (ባዮ ቴክኖሎጂ) የሰው ኃይል ለማፍራት ለ10 ዓመታት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚተገበር ረቂቅ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ላይ የትችትና ውይይት ዐውደ ጥናት ለሁለት ቀናት ተካሂዷል።

በውይይቱ የተሳተፉ የምርምር ተቋማት ባለድርሻ አካላት ለኢዜአ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የብዝሃ ሕይወት ሀብቷን በአግባቡ ለመጠቀም የጥበበ ሕይወት (ባዮ ቴክኖሎጂ) ምርምርን ማጠናከርና መተግበር ያስፈልጋታል።

በኢትዮጵያ የአካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪው አቶ አዱኛው አድማስ ዘመናዊ ባዮ ቴክኖሎጂ ወይም ጥበበ ሕይወት የዘረ-መል ምህንድስና መሆኑን ይገልጻሉ።

ለአብነትም የተለያዩ ባክቴሪዎችና ፈንገሶችን በመጠቀም የእጽዋት ብዝሃ ሕይወትን በተለያዩ የአየረ ንብረት ክልል እንዲላመዱ ማድረግ፣ የሰብል ምርታማነት መጨመርና ከተባይና በሽታ መከላከል እንደሚያስችል ያብራራሉ።

የጥበበ ሕይወት መተግበር አገሪቱ ካላት ብዝሃ ሕይወት አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰው፤ ጥበበ ሕይወት በግብርናና በኢንዱስትሪ ፖሊሲዎች የተቃኘ እንዲሆንም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተከለሰ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው ያምናሉ።

ጥበበ ሕይወት በየትኛውም ዘርፍ አስፈላጊ እንደሆነ የሚናገሩት ሌላው በኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ገነነ ተፈራም “ባዮ ቴክኖሎጂ በእርሻ፣ በጤና በአካባቢ ጥበቃና በብዝሃ ሕይወት ጥበቃም ትልቅ ጠቀሜታ አለው” ብለዋል።

ይህን ዘርፍ ማጠናከርና በትምህርት መስክ በቂና ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ሀብት በብዝሃ ሕይወት በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣት የጥበበ ሕይወት ድርሻዋን ማሳደግ ይገባታል ብለዋል።

ጥበበ ሕይወትን ወደመሬት ለማውረድ የሰው ሃይልና የምርምር ቤተ ሙከራ መሰረተ ልማት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ የ10 ዓመቱ ፍኖተ ካርታውም የጥበበ ህይወት ምሩቃን በቂ ክህሎት ይዘው እንዲወጡና አገራዊ እድል ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ዘሪሁን ከበደ እንዳሉት አዲሱ የጥበበ ህይወት ፍኖተ ካርታ  ከገበያው ጋር የተጣጣመውን የሰው ሃይል ለማፍራት ተግባራዊና ችግር ፈቺ ምርምር ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነ አንስተዋል።

በዚህም ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ድግሪ መርሃ ግብሮች ምሩቃን አስፈላጊውን ክህሎት ይዘው አንዲወጡ የሚያስችል እንደሆነ በመግለጽ፤ የተሻሻለው ፍኖተ ካርታ በሃሰቦችና ትችቶች ዳብሮ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች  በተጣጣመ መልኩ ተግበራዊ ይደረጋል ብለዋል።