ኅብረተሰባዊ ለውጥ በሚፈለገው ልክ የሚረጋገጠው የሴቶችን አቅም አውቆ በማሳተፍ ነው ---የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

76
ሐዋሳ ጥቅምት 23/2011 ኅብረተሰባዊ ለውጥ በሚፈለገው ልክ የሚረጋገጠው የሴቶችን አቅም አውቆ በማሳተፍ መሆኑን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዛሬ ገለጹ። የደኢህዴን/ኢህአዴግ  ሴቶች ሊግ  አራተኛ ጉባዔ ''የሴቶች አንድነትና የተደራጀ ትግል ለሁለንተናዊ ለውጥ!'' በሚል መሪ ሀሳብ በሐዋሳ ከተማ  ተጀምሯል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ደኢህዴን) ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በዚህ ወቅት እንዳሉት ኅብረተሰባዊ ለውጥ በሚፈለገው ልክ የሚረጋገጠው የለውጥ አራማጅና የለውጥ መሪ በመኖሩ ብቻ ሳይሆን፤ ሴቶች የለውጡ ተዋናይ ሲሆኑ ነው፡፡ የሴቶችን ተጨባጭ አቅምና ወሳኝነት ተረድቶ በአገር ግንባታ ሂደት ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ እንደሚያስፈልግም አቶ ሚሊዮን አመልክተዋል፡፡ የሴቶችን እኩልነት ማረጋገጥ ፣ በቂ እድል መስጠት ፣ ድጋፍና ክትትል ማድረግ ክልሉና አገሪቱ ከድህነትና ኋላቀርነት ጫና ማላቀቅ  እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም  የክልሉ መንግሥት ሴቶችን ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ለማሳተፍ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ የደኢህዴን ሊቀመንበርና የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው ጉባዔው ለሴቶች እንደ ነውርና ክልክል ይታዩ የነበሩ የኃላፊነት ቦታዎችና እርከኖች ሴቶች የሚችሉ መሆናቸውን በተረጋገጠበት ማግስት መሆኑ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ ለሴቶች የርዕሰ ብሄርነትና የፍትህና ፀጥታው ሴክተር ኃላፊነት በመሰጠቱ  ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ሊጉ የሴቶችን ሁለንተናዊ ትግል የተደራጀ ለማድረግና በዲሞክራሲያዊ፣ በመልካም አስተዳደርና በልማት ጉዳዮች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ሴቶች በድካማቸው ልክ  ተጠቃሚ በማድረግ ፣ በመብቶቻቸውና በህብረተሰባዊ ለውጥ  የመሪነት ሚና ተጫውቷል ብለዋል፡፡ ሴቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ በግብርናው መስክ ገቢያቸውን ማሳደግ የቻሉ ሲሆን፣ በትምህርትና በጤና አገልግሎት ረገድም የሴቷን ጫና መቀነስ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች እመርታዎች ቢኖሩም ስር ነቀል ለውጥ በማምጣት አሰራርን መቀየር እንደሚያስፈልግ ወይዘሮ ሙፈሪሃት አስገንዝበዋል፡፡ ለአራት ቀናት በሚካሄደው ጉባዔ ሊጉ አፈፃፀሙን ይገመግማል። በቀጣይ እቅድ ዙሪያ ይመክራል ተብሎ  ይጠበቃል፡፡ በጉባዔው ላይ የሊጉ አባላት፣ የአጋር ድርጅቶች ተወካዮችና እንግዶች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡ ሊጉ ጉባዔውን የሚያካሂደው ከሁለት እስከ ሁለት ዓመት ተኩል ባለጊዜ ውስጥ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም