በአፍሪካ የህፃናት ደህንነት አጠባበቅ አሁንም ብዙ ስራ እንደሚቀረው ተነገረ

73
አዲስ አበባ ጥቅምት 23/2011 በአፍሪካ የህፃናት ደህንነት አጠባበቅ ሞሪሺየስ የመጀመሪያውን ደረጃ ስትይዝ ኢትዮጵያ ደግሞ አርባ ሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አንድ ሪፖርት አመለከተ። የ'አፍሪካ ቻይልድ ፖሊሲ ፎረም' የ2018 የአፍሪካ አገራት ለህፃናት ደህንነት ያደረጉትን እንክብካቤ አስመልክቶ ያወጣው ሪፖርት ነው ይህን ያለው። ለህፃናት ተስማሚነት መሰረት የሆኑ የህፃናት ከለላ፣ አቅርቦትና አሳታፊነት በአመላካችነት ለሪፖርቱ መጠቀማቸውን ነው የተገለፀው። ለህፃናት መብት መጠበቅ የሚደረጉ የህግና የፖሊሲ ከለላዎች፣ ተገቢ የሆነ የአመጋገብ ስርዓት፣ ለህፃናት የሚደረግ የጤና አጠባበቅ፣ ትምህርትና የልደት ምዝገባዎችም ለህፃናት ደህንነት አጠባበቅ በሪፖርቱ እንደመስፈርትነት ከተጠቀሱ መካከል ይገኝበታል። ለህፃናት የሚመደብ በጀት በየአገራቱ ቢለያይም በአማካይ አፍሪካ 4 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆነውን በጀቷን ብቻ ነው ከህፃናት ጋር ተያያዥ ለሆነ ጉዳይ የምታውለው ሲል ሪፖርቱ ያትታል። በተመሳሳይ ለህፃናት የጤና ወጪዎች 6 ነጥብ 3 በመቶ በጀት ብቻ ተግባር ላይ ይውላል። የአፍሪካ ቻይልድ ፖሊሲ ፎረም መስራችና ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሰፋ በቀለ እንደተናገሩት አፍሪካ የመጀመሪያ ትምህርት ተደራሽነትን እያሳደገች ያለች ብትሆንም ተማሪዎቹ ትምህርት ቤት ሄደው ከመመለስ በቀር በየእድሜያቸው ማግኘት ያለባቸውን እውቀት እየቀሰሙ አይደለም ብለዋል። በተጨማሪም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአግባቡ ተምረው የማያጠናቅቁም አያሌ እንደሆኑ ተናግረዋል። በአለም አቀፍ ስታንዳርድ መሰረት ከ12 አመት በታች ያሉ ህፃናት በወንጀል መጠየቅ የለባቸውም ቢልም ከሰባት ጀምሮ ለተጠያቂነት የሚያቀርቡ መኖራቸውን ሪፖርቱ ይገልፃል። ባለፉት ሃያ አመታት በህፃናት መብትና ደህንነት አጠባበቅ ላይ ከነበሩ ተግባራት አሁን መሻሻሎች ቢኖሩም እያደገ ካለው የአፍሪካ የህዝብ ቁጥር አንፃር ወደፊት በተሻለ መስራት ካልተቻለ ስጋት ሊሆን እንደሚችልም ሪፖርቱ ጠቅሷል። በዚህም መሰረት ሞሪሺየስ ከ52 የአፍሪካ አገራት በአንፃራዊነት የህፃናት ደህንነትን ትጠብቃለች ለህፃናትም ተስማሚ ናት በሚል ሪፖርቱ የመጀመሪያውን ደረጃ ሰጥቷታል። ኢትዮጵያም ከመጨረሻዎቹ 10ኛውን ደረጃ ስትይዝ ለህፃናት ያላት አያያዝና ደህንነታቸውን ከመጠበቅ አንፃር ዝቅተኛ ከተባሉ አገራት ተርታ ተሰልፋለች። በምግብ እጥረት ከሚከሰተው የመቀንጨር ችግር ጋርም ተያይዞ ምርታማ ስለማይሆኑ ከአመታዊ አገራዊ ምርቷ ከ16 በመቶ በላይ እንደምታጣ ሪፖርቱ ያሳያል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለነዚህ ደህንነቶች መጠበቅ መሰረት ነው በተባለው የልደት ምዝገባ ሁለት ነጥብ ሰባት በመቶ ለሚሆኑ ህፃናት ብቻ ምዝገባ በማካሄድ ከሁሉም አገራት አንሳ ተገኝታለች። በአፍሪካ ህብረት የማህበራዊ ዘርፍ ኮሚሽነር አሚራ ኤልፋዲል እንዳሉት ህብረቱ በ2063 አጀንዳ ሪፖርቱ በጣም ጠቃሚ መሆኑን ገልፀው ይህን መሰረት በማድረግ ተጨማሪ ጥናት እንደሚደረግ ገልፀዋል። በጉዳዩ ላይ ከአጠቃላይ አባል አገራት ጋር እንደሚወያዩበትም አስታውቀዋል።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም