የአሜሪካን መንግስት ለጅማ አባጅፍር ቤተመንግሰት ዕድሳት ድጋፋ አደረገ

89
ጅማ ጥቅምት 23/2011 የአሜሪካን መንግስት ለጅማ አባጅፍር ቤተመንግሰት ዕድሳት የሚውል 125 ሺህ ዶላር ድጋፋ አደረገ። በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነር  ዛሬ በአባጅፋር ቤተመንግስት በመገኘት የገንዝብ ድጋፉን አድርገዋል። ቤተ መንግስቱ የታሪክ፣የማንነትና የባህል መገለጫ በመሆኑ ተንከባክቦ ለማቆየት የገንዘብ ድጋፉ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አምባሳደሩ  ተናግረዋል። በድጋፍ አሰጣጡ ስነስርዓት የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚንስተሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው" የጅማ ቤተመንግስት የኢትዮጵያ   አኩሪ ቅርስ በመሆኑ አስፈላጊው እንክብካቤ ይደረግለታል" ብለዋል። የጅማው ንጉስ አባጅፋር ትተው ያለፉት ቤተመንግስቱን ብቻ ሳይሆን ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነትና ተቻችሎ የመኖርን ኢትዮጵዊነትን ባህል ጭምር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከንጉስ አባጅፋር የወረስነውን  ይህንን መልካም ባህል ለአዲሱ ትውልድ ለማስተላለፍ የቤተ መንግስቱ መታደስ እንደሚያስፈልግ አመልክተው እድሳቱ በቀጣዮቹ 18  ወራት ውስጥ በማጠናቀቅ ለጎብኝዎች ክፍት ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መኪዩ መሐመድ በቤተመንግስቱ ላይ በደረሰው ጉዳት የአካባቢው ህዝብ  ቅሬታ ማሳደሩን ጠቁመው አሁን ለቤተ መንግስቱ የተሰጠው ትኩረት ቅርሱን ከጉዳት እንደሚታደግ ገልጸዋል። የጅማ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጀሃድ መሃመድ በሰጡት አስተያየት የጅማ አባጅፋር ቤተመንግስት ተጎድቶ በማየታቸው ማዘናቸውንና አሁን ለመታደስ ዝግጅት መደረጉ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል። የጅማ አባጅፋር ቤተመንግስት በእርጅና ምክንያት በደረሰበት ጉዳት ላለፉት ሰባት ወራት ለጎብኝዎች ዝግ ሆኖ በሚታደሰበት ሁኔታ ላይ በጅማና በአዲስ አባባ የኒቨርስቲዎች ጥናት ሲካሄድ መቆይቱ ከጅማ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም