በቀን ከ1 ሺህ 300 በላይ ዜጎች በህገ ወጥ ቪዛ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሀገር ይወጣሉ-ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

71
አዲስ አበባ ጥቅምት 23/2011 ህገ ወጥ በሆነ ቪዛ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል በቀን ከ1ሺህ 300 በላይ ዜጎች ወደ ተለያዩ አረብ አገራት እንደሚጓዙ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። የዚህ ዓይነቱ ህገ ወጥ ጉዞም ከሰኞ ጀምሮ ክልከላ ማደረጉንም አስታውቋል። ሚኒስቴሩ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዙሪያ ያተኮረ ምክክር ካበላድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል። የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ይርጋለም በዚሁ ግዜ እንደገለጹት ዜጎች በህገ ወጥ መንገድ በጂግጂጋ፣ በሞያሌ፣ መተማና ሚሌ ጋላፊ በህገ ወጥ ደላላዎች አማካኝነት የሰዎች ዝውውር በስፋት የሚደረጉባቸው ስፍራዎች ናቸው ብለዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የተለያዩ የቪዛ አይነቶችን በመጠቀም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ዜጎች ህገ ወጥ የሆነ ጉዞን እያደረጉ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አንዱ ምክንያት እየሆነ መምጣቱን በመግለጽ። በዋናነትም የህክምና፣ የጉብኝት፣ የዘመድ ጥየቃና የንግድ ቪዛዎችን በህገ ወጥ መንገድ በማስወጣት በርካታ ዜጎች እየተጓጓዙ በመሆኑ ለህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ድርሻው የጎላ እንዲሆን አድርጓል ነው። በተጨማሪም ደላሎች ዜጎችን በአየር መንገዱ እንዲጓጓዙ ሲያደርጉ ህጋዊ ጉዞ እንደሆነ በማስመሰል ተጓዦች ለእንግልትና ለአላስፈላጊ ችግር እንዲጋለጡ እያደረገ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። በዚህም ዜጎች ለእስር፣ ለአካል መጉደልና ለአእምሮ መታወክ፣ ለአስከፊ ህይወትና ለሞት እየተዳረጉ ከመሆኑም ባሻገር ህጋዊ ከለላ እንዳያገኙም ሆኗል። በዚህም የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚገታና ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ግብረ ሃይል የተቋቋመ በመሆኑ ከሰኞ ጀምሮ አስፈላጊው ክትትል የሚደረግ መሆኑንና ህገ ወጥ ቪዛዎች የተገኘባቸው ዜጎች ክልከላ እንደሚደረግባቸው ነው የተናገሩት። መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ቁጥጥሩን የሚያጠናክር መሆኑንና ተጠያቂዎችንም ለህግ ለማቅረብ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል። ዜጎች መንግስት በህጋዊ የስራ ስምሪት በተዋዋለባቸው ሳውዲ ዓረቢያ፣ ዮርዳኖስና ኳታር በህጋዊ መንገድ ተዘዋውረው እንዲሰሩ ዳይሬክተሩ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም