ታዳጊዋን አስገድዶ የደፈረው በ6 ዓመት ከ5 ወር ጽኑ አስራት ተቀጣ - ኢዜአ አማርኛ
ታዳጊዋን አስገድዶ የደፈረው በ6 ዓመት ከ5 ወር ጽኑ አስራት ተቀጣ
60
አምቦ ጥቅምት 23/2011 ታዳጊዋን አስገድዶ ደፍሯል የተባለውን ግለሰብ በስድስት ዓመት ከ5 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን በምዕራብ ሸዋ ዞን የአቡነ ግንደበረት ወረዳ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡ የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ባይሳ ገላና እንደገለጹት ወንጀሉ መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም የተፈጸመው በወረዳው ኢርጃጆ ቀበሌ ልዩ ቦታው ጂቢቾ ገበሬ ማህበር ውስጥ ነው፡፡ ተከሳሽ ሰቦና ቱቻ ቆለሳ የተባለው ግለሰብ የአካባቢው ልጅ የሆነችውን የ16 ዓመት ታዳጊ በዕለቱ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት አካባቢ ከትምህርት ቤት ስትመጣ በጉልበት በማስፈራራትና የባቄላ ቡቃያ ውስጥ ስቦ በማስገባት ጥቃት ፈጽሞባታል፡፡ አቶ ባይሳ እንዳሉት የወረዳው አቃቤ ህግ በግለሰቡ ላይ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ክስ መስርቶበት ተከሳሹ ድርጊቱን መፈጸሙን አምኖ ተቀብሏል። ግለሰቡ ቀደም ሲል የወንጀል ሪክርድ የሌለበት መሆኑም እንደ አንድ ቅጣት ማቅለያ ተይዞለታል፡፡ የግራቀኙን ክርክር ያዳመጠው የወረዳው ፍርድ ቤት ጥቅምት 22 ቀን 2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሹን ጥፋተኛ ነው በማለት በእስራት እንዲቀጣ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በእዚህ መሰረት ሌሎችን ያስጠነቅቃል ወንጀለኛውንም ያስተምራል በሚል ተከሳሹን በስድስት ዓመት ከ5 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን አቶ ባይሳ አስረድተዋል፡፡