ሚኒስቴሩ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃን ለማጠናከር መዘጋጀቱን ገለጸ

79
አዳማ ጥቅምት 23/2011 ለግብርናው ዕድገት ቀጣይነት መደላድል ለመፍጠር የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃን ሳይንሳዊ አሰራር ለማጠናከር መዘጋጀቱን የግብርናና እንስሳት ሀብት ልማት ሚኒስቴር ገለጸ። ሚንስቴሩ የ2011 በጀት ዓመት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃን ለማከናወን የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የዝግጅት ምዕራፍ አፈጻጸምን በአዳማ ከተማ እየገመገመ ነው። የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃን ወደ ላቀ ደረጃ  በማሸጋገር የአርሶ አደሩን የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጥ የበጀት ዓመቱ ትኩረት ነው፡፡ የአፈር ለምነት በመጠበቅ ምርትና ምርታማነትን በእጥፍ ማሳደግም እንዲሁ፡፡ የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ሚንስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ በግምገማው መድረክ እንዳገለጹት በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ላይ አርሶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ከእቅድ ዝግጅት ጀምሮ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖረው እየተደረገ ነው፡፡ ለዚህም የማስፈጸም አቅምን በማጎልበትና ፈጻሚውን  በማብቃት ለተግባራዊነቱ እንዲረባረብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተያዘው የበጀት ዓመት ከ2 ሚሊዮን ሄክታር ያላነሰ መሬት  በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት  ለመሸፈን መታቀዱን ያመለከቱት ሚኒስትር ዴኤታው ፣ከ1 ሚሊዮን በላይ በአሲድ የተጠቃ መሬት የማከምና ምርታማነታቸውን የማሳደግ ሥራ እንደሚከናወን አስረድተዋል። እንደ ዶክተር ካባ ገለጻ እቅዱን ስኬታማ ለማድረግ የህዝብ ንቅናቄ ከመፍጠር ፣ባለሙያዎችንና አመራሮችን በሳይንሳዊ አየተፈጥሮ ሀብት ልማትና አያያዝ ዙሪያ ግንዛቤ ማስጨበጥ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ተከናውኗል። "ፈፃሚው ህብረተሰብ በተራራ ላይ በሚሰሩ የአፈርና ውሃ መጠበቂያና በጠረዼዛ እርከኖች አተገባበር ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ እየሰራን ነው" ብለዋል። የተጎዳ መሬትን  ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነፃ አድርጎ የማካለል፣በዘርፉ አማራጭ የሥራ እድሎች በስፋት የሚፈጠሩበትን አሰራሮች እያመቻቹ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት የተሰሩ  የተፋሰስ ልማት የሥነ ህይወታዊና አካላዊ ሁኔታቸውን ፈትሾ  መንከባከብ፣ለእርከኖች እድሳትና ጥገና ማድርግ ሌላው በእቅዱ ትኩረት ያገኙ ሥራዎች ናቸው። በበጀት ዓመት የሚከናወኑ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት፣የአፈር ውሃ እቀባን ሥራን ለግብርናው ዘርፍ ልማትና ዕድገት ቀጣይነት ምቹ ሁኔታ  መፍጠር በሚችሉበት መልኩ ለማጠናከር ዝግጅት መደረጉን   ዶክተር ካባ አብራርተዋል፡፡ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራን በተሻለ ደረጃ ለመፈፀም  ለ3ሺህ 760 ተፋሰሶችን ጥናትና ዲዛይን በማዘጋጀት ወደ ተግባር ምዕራፍ መግባታቸውን የገለፁት ደግሞ በደቡብ ህዝቦች ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የዘርፉ ባለሙያ አቶ ቦጋለ ሌንጫ ናቸው። በክልሉ በበጀት ዓመቱ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጥ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለማከናወን ታቅዷል፡፡ በትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የሆርቲካልቸርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ በርሁን አረጋዊ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ ከ100ሺህ ሄክታር በላይ አካላዊናሥነ ህይወታዊ ሥራን ለማከናወን ማቀዳቸውን ገልጸዋል። "ከ120 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ችግኞች እየተዘጋጁ ነው" ያሉት ዳይሬክተሩ ከዚህም 24 ሚሊዮን  የሚሆኑት የቀርካሃና የጃትሮፋ ተክል መሆኑን ገልጸዋል። በአዳማ ከተማ ለሶስት ቀናት በሚቆየው መድረክ ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮችና ከዘጠኙ ክልሎች የተወጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮች እየተሳተፉ ነው።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም