የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኦዴግ/ አመራሮች አዲስ አበባ ገቡ

149
አዲስ አበባ ግንቦት 15/2010 የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኦዴግ/ አመራሮች ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ አመራሮቹ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት ጉዳዮች አማካሪ አቶ አባ ዱላ ገመዳና የመንግስት ኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የትኛውም በውጭ አገር መቀመጫውን ያደረገ የፖሊቲካ ፓርቲ ወደ አገሩ መጥቶ በሰለማዊ መንገድ አንዲታገል ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ መቀመጫውን ውጭ አገር ያደረገውና በቅርብ ጊዜ ራሱን ከኦነግ ነጥሎ ኦዴግ በሚል ስያሜ የተመሰረተው ፓርቲ ለድርድር ቃዳሚ ሆኗል ። በዚህም መሰረት በድርጀቱ ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ የተመራውና ምክትሉን ጨምሮ አምስት ከፍተኛ አመራሮች ያሉበት ልዑክ ዛሬ ማለዳ አዲሰ አበባ ገብተዋል። አቶ ሌንጮ በዚሁ ወቅት ለመገናኛ ብዙሃን ሲናገሩ አመጣጣቸው አገር ውስጥ ያለውን ሁኔታ በቅርበት ለማጤንና የወደፊት አቅጣጫውን ለመወሰን ነው ብለዋል። ከአገር ውጭ ሆነው በሚደረግ ትግል እንደማያምኑ የተናገሩት የፓርቲው ሊቀመንበር ከዚህ በፊትም ሁኔታዎች ባለመመቻቸታቸው ውጭ እንደቆዩ ነው የገለጹት፡፡ የድርጅቱ ሊቀመንበር አሁን በሃገሪቱ እየታየ ባለው የለውጥ መንፈስም መደሰታቸውን ገልጸዋል። አሁን የመጡት ሁኔታዎችን ለመቃኘትና ከተለያዩ አካላት ጋር ለመመካከር ቢሆንም ፓርቲያቸው ወደፊት እንደ አገር ውስጥ ፓርቲ ተመዝግቦ፣ ብቻውንም ሆነ ከሌሎች ጋር በመጣመር ለመንቀሳቀስ ፍላጎት እንዳላቸውም ጠቁመዋል። ለአገር ለውጥ ለማምጣት የሚፈልግ የትኛውም የፖሊቲካ ፓርቲ በሰላማዊ መንገድ መታገልን ቀዳሚው አማራጭ ማድረግ እንደሚገባም ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት ጉዳዮች አማካሪ አቶ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው ከአሁን በኋላ ትግል መሆን ያለበት በሰላማዊ መንገድና በሃስብ ብቻ መሆን እንደሚገባና ኦዴግ ለድርድር መምጣቱም ፈር ቀዳጅና ምሳሌ የሆነ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል። መንግስት ከዚህ በኋላ ''የሃሳብና የፖሊሲ ልዩነት ሊያጣላን አይገባም'' የሚል ጽኑ አቋም እንደያዘ በመግለጽም ለአገር የሚጠቅም የተሻለ ሃሳብ አለኝ ከሚሉት ሁሉም ጋር አብሮ ለመስራት መንግስት ዝገጁ መሆኑን ገልዋል። ለቀሩትም የኦዴግን መንገድ እንዲከተሉ ጥሪ አስተላፍዋል። የፓርቲው አመራሮች ከተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም