በመዲናዋ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ቅንጅታዊ አሰራር ሊኖር ይገባል - አስተያየት ሰጪዎች

54
ጥቅምት 23/2011 በአዲስ አበባ ከተማ እያገረሸ የመጣውን የኤች አይ ቪ ኤድስ ሻይረስ ስርጭትን ለመግታት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትና ህብረተሰቡ በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ። ከዚህ በፊት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በተሰራው ስራ የተገኘው ውጤት መዘናጋትን  በመፍጠሩ በከተማዋ  የበሽታው ስርጭት መባባሱን ነው የአዲስ አበባ  የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ፅሕፈት ቤት የገለፀው፡፡ በሚመለከታቸው የመንግስት አካላትና በህብረተሰቡ እየተስተዋለ ያለው መዘናጋት የቫይረሱ ስርጭት እንዲጨምር አስተዋጽኦ አድርጓል ያሉት አቶ ግርማ ብሩ ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት። በሽታው እያስከተለ ያለውን ሀገራዊ  ቀውስ ለመቀልበስ  በተለይም  የፖለቲካው አመራር ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ያሉት  አቶ ግርማ ከሌሎች የልማት አጀንዳዎች ባልተናነሰ ትኩረት ሊደረግበት ይገባልም ብለዋል። የአዲስ አበባ አረጋውያን ማህበር  ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ በቀለ በበኩላቸው   ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ የማሕበረሰብ  ክፍሎች  በተለይ  ወጣቶች የበለጠ ተጋላጭ እንዳይሆኑ  የቤተሰብ ምክር ወሳኝ መሆኑን ነው የጠቆሙት። የሃይማኖት ተቋማት ከመንፈሳዊ አስተምህሮት ጎን ለጎን የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል  የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባቸው የተናገሩት በአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሚሰሩት ሼክ ሰማን መሃመድ ናቸው፡፡ በመዲናዋ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ስርጭትን  ለመከላከል እና ለመቆጣጠር  ሁሉም የህብረተሰብ  ክፍል ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባም ሼክ ሰማን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ አካል ጉዳተኞች ለኤች አይ ቪ ኤድስ የመጋለጥ እድላቸው አናሳ ነው በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ በእነዚህ አካላት ላይ ጉዳት ሲደርስባቸው  መቆየቱን የተናገሩት የአዲስ አበባ ከተማ አካል ጉዳተኞች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ንጉሴ ግደይ ናቸው፡፡ በከተማዋ የሚገኙ ቀላል የማይባሉ አካል ጉዳተኞች ከኤች አይቪ ኤድስ ቫይረስ ጋር እንደሚኖሩ የገለፁት አቶ ንጉሴ  ቫረሱን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በሚደርገው ጥረት ለአካል ጉዳተኞችም ልዩ ትኩረት ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። በከተማ ደረጃ በአሁኑ ወቅት የበሽታው ስርጭት 3.4 መድረሱን  የገለፁት የጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ ሲስተር ብርዛፍ ገብሩ ቫይረሱ በስፋት ከተሰራጨባቸው ከተሞች መካከል አዲስ አበባ ከጋምቤላ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። የበሽታው ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት ሲስተር ብርዛፍ በተለይም ከ15 እስከ 24 ዓመት ዕድሜ ክልል ውሰጥ የሚገኙ ወጣቶች የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ ይስተዋላል ነው ያሉት። ጽህፈት ቤቱ በተለይም ተጋላጭ የሆኑ እና የተለየ ትኩረት የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት ከተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የህብረተሰብ ክፍሎችና አደረጃጀቶች ጋር በመቀናጀት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እየሰራ እንደሆነ ሃላፊዋ  ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም