የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ማመንጫ፣ ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ዕቃዎች አምራቾች ማህበር ተመሰረተ

1503

አዲስ አበባ ጥቅምት 22/2011 የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ማመንጫ፣ ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ዕቃዎች አምራቾች ማህበር ተመሰረተ።

መንግስት ለማህበሩ መጠናከር ድጋፍ ያደርጋል ተብሏል።

ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ማመንጫ፣ ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ዕቃዎች አምራች ኢንዱስትሪዎች ማህበር በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ተመስርቷል።

የማህበሩ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት አቶ ወንድወሰን በላይ እንደገለፁት፤ ማህበሩ የኤሌክትሪክ ኃይል ኢንዱስትሪውን ለማዘመን በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾች በጋራ እንዲሰሩ ዕድል ለመፍጠር ያለመ ነው።

በኤሌክትሪክ ማመንጫ፣ ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ዕቃዎች አምራቾች ጥራት ያለው ዕቃ ለማምረትና በመካከላቸው የልምድና የዕውቀት ልውውጥ እንዲኖር ማድረግ የማህበሩ ዋና ዓላማ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በዘርፉ የሚያጋጥሙ የአሰራርና የመቀናጀት ችግሮች ለመቅረፍ በማህበር በመደራጀት ከመንግስት ጋር ለመስራት አመቺ ዕድል እንደሚፈጠርም አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል ኢንዱስትሪ የተሰማሩ ባለሃብቶች ተቀናጅተውና ተደጋግፈው ከሰሩ በአገር ውስጥ የተሻለ አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሆነው በመቅረብ አቅምን በማሳደግ ወደ ወጭ ገበያ መዝለቅ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

የማህበሩ የክብር አባል የሆኑት የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መሀንዲሶች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃኑ ግዛቸው በበኩላቸው የማህበሩ መመስረት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚረዳ ገልጸዋል።

በዘርፉ ያለውን ዕውቀት ለማስፋትና ሽግግር ለማድረግ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የተቀናጀ ትስስር ለመፍጠር በማህበር መደራጀት የተሻለ እንደሆነ አመልክተዋል።

በአገር ውስጥ የሚገኙ በርካታ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ‘ጥራት የለውም’ በማለት በአገር ውስጥ የሚመረት የኤሌክትሪክ ዕቃዎች እንደማይጠቀሙ የጠቆሙት ዶክተር ብርሃኑ ማህበሩ ጥራት ያለው ዕቃ እንዲመረት የመስራት አቅምን ለማጎልበት እገዛ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በአገር ውስጥ የተመረተ ምርት ሁሉ ጥራት እንደሌለው አድርጎ የመመልከትን ችግር ለመፍታትም በማህበር ተደራጅቶ መንቀሳቀስ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

በማህበሩ ምስረታ የተገኙት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዮሃንስ ድንቃየሁ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የጀመረችው ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት አጠናክሮ ለማስቀጠል የኢንዱስትሪው ዘርፍ መጠናከር ዋናው መሰረት ነው።

ይሄን እውን ለማድረግም በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾች አቅም እየፈጠሩ ጥራት ያለውና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ ዕቃ ማምረት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ለዚህም የተመሰረተው ማህበር የኤሌክትሪክ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማጎልበትና ለማዘመን እንዲሁም በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን እየነቀሱ ለመፍታት የራሱን ሚና ይጫወታል ሲሉ ተናግረዋል።

መንግስትም ለማህበሩ መጠናከርና መጎልበት ድጋፎች እንደሚያደርግም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ማመንጫ፣ ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ዕቃዎች አምራቾች ማህበር ስድስት አባላት ያሉት የሥራ አመራር ቦርድ ተሰይሟል።