በአገሪቱ በሥራ ላይ ያለው ሥርዓተ ትምህርት ያሉበትን ችግሮች ለማስወገድ ኅብረተሰቡ ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል---ዶክተር ጥላዬ

60
አዳማ ጥቅምት 22/2011 በአገሪቱ በሥራ ላይ ያለውን ሥርዓተ ትምህርት ያሉበትን ችግሮች ለማስወገድ ኅብረተሰቡ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትሩ አሳሰቡ። በትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ጥናት ዙሪያ ግብዓት ለማሰባሰብ የተዘጋጀ አገር አቀፍ የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው። የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በመድረኩ ላይ እንዳስገነዘቡት ሥርዓተ ትምህርቱን ካሉበት ችግሮች ለማውጣት ሕዝቡ ተሳትፎ  ማድረግ ይጠበቅበታል። ፖሊሲው ባለፉት 24 ዓመታት ሥራ ላይ ቢውልም፤ ለሁሉም ሕፃናትና ወጣቶች ትምህርትና ስልጠና ማዳረስ አልተቻለም ብለዋል። በሀገሪቱ ከሚገኙ ህፃናት መካከል 55 በመቶ የሚሆኑት የትምህርት እድል ተጠቃሚ አልሆኑም ያሉት ሚኒስትሩ በተለይ ምቹ፣ ሳቢና ማራኪ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተቋማት ተደራሽነት ላይ ውስንነቶች እንዳሉ ይናገራሉ። እንዲሁም የሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞችና አይነ ስውራን የትምህርት ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑንም አስታውቀዋል። በቴክኒክና ሙያ፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ብቁ፣ ተወዳዳሪ፣ ችግር ፈቺ፣ ሥራ ፈጣሪና ሀገሩን የሚወድ ትውልድ በማፍራቱ በኩልም ችግሩ የሰፋ መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል። በሁሉም ደረጃ በሚገኙ የትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል አሳሳቢ እንደሆነም ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ፕሮግራም በአግባቡ ያልተተገበረና በውሸት መረጃ የታጨቀ ሪፖርት ከአስፈጻሚው አካል ለሚኒስትቴሩና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲቀርብ መቆየቱንም አውስተዋል። ፖሊሲው ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ ውስብስብና መፍትሄ የሚፈልግ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል። በመሆኑም በዘርፉ ያለውን ሥር የሰደደ ችግር ለማቃለል ባለፉት ሶስት ዓመታት ለተዘጋጀው ፍኖተ-ካርታ ኅብረተሰቡ የተሟላ ግብዓት በመስጠት እንዲያዳብረው አሳስበዋል። ለፍኖተ ካርታ ግብዓት የማሰባሰቡ ሥራ ተጠናቆ ሲጸድቅ ለሚቀጥሉት 15 ዓመታት ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዶክተር ጥላዬ አብራርተዋል። የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ መሐመድ አህመድ በበኩላቸው በሀገሪቱ ዋና ዋና የትምህርትና ስልጠና ችግሮችና ተግዳሮቶች ተለይተው ከቀረቡት ምክረ ሀሳቦች መካከል በትምህርት ፍልስፍናው ዜጎች በራሳቸው የሚተማመኑ፣ብቁና በምክንያታዊ ትንተናና በውይይት የሚያምኑ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ብቁ ዜጋ አድርጎ አጠቃላይ ስብእናቸውን መገንባት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል። በትምህርት መዋቅር፣ በመምህራን ዝግጅትና ምልመላ፣ በአጠቃላይ ትምህርት፣ በትምህርት ስልጠና ቋንቋ፣ በሥርዓተትምህርት ይዘቶችና በሌሎችም ርዕሶች ላይ ያተኮሩ ምክረ ሃሳቦችንም አቅርበዋል። ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው በዚሁ መድረክ ላይ ከሁለቱ መስተዳድሮችና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች አባገዳዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም