አርሶ አደሮቹ ቡና በቀጥታ ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ በተፈጠረላቸው ዕድል ተጠቃሚ አልሆንም አሉ

98
ዲላ ጥቅምት 22/2011 ቡና በቀጥታ ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ በተፈጠረላቸው ዕድል የገበያ ትስስር ችግር ስላልተፈጠረላቸው ተጠቃሚ እንዳልሆኑ የጌዴኦ ዞን የቡና አምራች አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡ መንግሥት ከሁለት ሄክታር መሬት በላይ የሚያለሙ አርሶ አደሮች ምርታቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የላኪነት ብቃት ማረጋገጫ የሚያገኙበት  ዓዋጅ አውጥቷል። አርሶ አደሮቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ቡና አምራች አርሶ አደሮች ምርታቸውን በጥራት አዘጋጅተው ለውጭ ገበያ በቀጥታ  በማቅረብ ተጠቃሚ አልሆኑም፡፡ የገበያ ትስስር ባለመፈጠሩም የጥቅሙ ተቋዳሽ መሆን አልቻልንም  ይላሉ፡፡ በኮቾሬ ወረዳ በ12 ሄክታር መሬት ላይ ቡና የሚያለሙት አርሶ አደር ታደሰ ኮኖ የቡና ማሳ ተለክቶ፣ ምርታማነታቸውና የማሳ አያያዛቸው በባለሙያዎች ተገምግሞ ባለፈው ዓመት ያመረቱትን ቡና በጥራት አዘጋጅተው በቀጥታ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ  ፈቃድ አግኝተዋል ፡፡ አምና ከሰበሰቡት ምርት በደረጃ አንድ የሚመደብ 13 ሺህ 110 ኪሎ ግራም ያልታጠበ ቡና ቢያዘጋጁም፤እስካሁን ገዢ እንዳላገኙ ይናገራሉ፡፡ ''ፈቃዱን ስናገኝ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ትችላላችሁ እንባል እንጂ፤ ስለ አሻሻጡ ምንም ልምድ የለንም'' የሚሉት አርሶ አደር ታደሰ የገበያ ትስስር ስላልተፈጠረላቸው ተስፋ ያደረጉበትን ጥቅም ሳያገኙ ቀርቻለሁ ይላሉ፡፡ መንግሥት በገበያው  ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያመቻቸላቸው ዕድል የተሻለ ገቢ ከማስገኘቱም ባሻገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩት የገለጹት በዲላ ዙሪያ ወረዳ አርሶአደር ዳንኤል ሾጦጦ ናቸው፡፡ በሁለት ነጥብ ስምንት ሄክታር ላይ ቡና እንደሚያለሙና መንግሥት የዘረጋው አሰራር የቡና ምርታማነት ማሻሻያ ሥራቸውን አጠናክረው ለመቀጠል እንዳበረታታቸው ገልጸዋል፡፡ ሆኖም በ2010 ያመረቱትን ቡና ለውጭ ገበያ እንዲውል ናሙና  ቢልኩም፤ እስካሁን ገዢ እንዳላገኙ ይናገራሉ፡፡ በንግድ ሥራ ላይ የዳበረ ልምድ እንደሌላቸው የሚናገሩት አርሶ አደር፣''መንግሥት ዕድሉን እንደሰጠን ሁሉ የገበያውንም ችግር ሊፈታልን ይገባል''ይላሉ፡፡ በወናጎ ወረዳ በስድስት ሄክታር ላይ ቡና የሚያለሙት አርሶ አደር ዘለሉ አራርሶ ደግሞ ከዚህ በፊትም ቡናቸውን በይርጋጨፌ ቡና ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን በኩል በስማቸው ለውጭ ገበያ የማቅረብ ልምድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በቀጥታ ለውጭ ገበያ የማቅረብ ፈቃድ ቢሰጣቸውም፤ ገዢ ባለማግኘታቸው በዩኒየኑ በኩል ኮሚሽን ከፍለው በአደራ ለመሸጥ  መገደደዳቸውን አስረድተዋል ፡፡ መንግሥት የገበያውን ችግር ከፈታላቸው ከዚህ ቀደም ከምርታቸው ካገኙት አንድ ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አገኛለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል ፡፡ የጌዴኦ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ የቡናና ሻይ ቅመማ-ቅመም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አድማሱ ተፈራ መንግሥት የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ባወጣው ዓዋጅ ባለፈው የምርት ዘመን 203 አርሶ አደሮች ምርታቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የላኪነት ብቃት ማረጋገጫ ማግኘታቸውን  አስታውቀዋል ፡፡ ነገር ግን አብዛኛዎቹ አርሶ አደሮች ሂደቱን ከጀመሩ በኋላ የገበያ ችግር እንደገጠማቸው ተናግረዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ከመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር ጊዜያዊ የመፍትሔ እርምጃዎች ወስደናል ያሉት ኃላፊው፣አርሶ አደሮቹ የላኪነት ፈቃድ ቢኖራቸውም፤ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቡናቸውን የሚሸጡበት መንገድ መመቻቸቱን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም በይርጋጨፌ ቡና ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየንና በሌሎች ላኪ ድርጅቶች አማካይነት በኮሚሽን ክፍያ እንዲልኩ መደረጉንም አብራርተዋል ፡፡ከመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን አቶ አድማሱ አብራርተዋል፡፡ በገበያ ትስስር ዘርፍ የሚሰሩ ድርጅቶች የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶላቸው እንዲሰሩ አርሶ አደሮቹን በውጭ ካሉ ገዢዎች ጋር በቀጥታ ለማገናኘት በጥናት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡ በቀጣይም አርሶ አደሮቹ በግልም ሆነ በወኪሎቻቸው አማካይነት በውጭ የሚካሄዱ ኤግዚቢሽኖች ላይ ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁ ጥረት እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ አድማሱ ገለፃ እስካሁን ከ85 የሚበልጡ አርሶ አደሮች በአገር ውስጥና በውጭ ገበያ ምርታቸውን በመሸጥ ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አግኝተዋል ፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2009ያወጣው የቡና ግብይትና ጥራት ቁጥጥር ዓዋጅ ሁለት ሄክታርና ከዚያ በላይ በሆነ መሬት ላይ ቡና የሚያለሙ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ ይደነግጋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም