እየተባባሰ የመጣውን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለመከላከል የቁጥጥር ስራ እያከናወነ መሆኑን ፌዴራል ፖሊስ አመለከተ

84
አዲስ አበባ ጥቅምት 22/2011 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ህገ ወጥ የጦር መሰሪያ ዝውውር እየጨመረ በመምጣቱ ለአገሪቱ ሰላምና ደህንነት አሳሳቢ ሆኗል። ይህን ችግር ለመከላከል የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከምንጊዜውም የበላይ በሁሉም የአገሪቱ መግቢያና መውጫ በሮች ላይ የተጠናከረ ፍተሻና ቁጥጥር እያደረገ እንደሚገኝ አመልክቷል። ኮሚሽኑ በተለይ በሱዳን በኩል የሚመጣውን ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለመከላከል ከአገሪቱ የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው። በኮሚሽኑ የወንጀል መከላከል ዘርፍ የፈጥኖ ደራሽ ዳይሬክተር ኮማንደር አይሳ ዳመና ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የህገወጥ ጦር መሳሪያ ዝውውሩ በነዳጅ ቦቴዎች ላይ ማዘዋወር እየተለመደ በመምጣቱ ኮሚሽኑ ወንጀሉን ለመከላከል ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው። ከሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 20 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ 3 ብሬን፣ 167 ክላሽ፣ 2ሺህ335 ሽጉጥ፣ 13 ቦምብ በአጠቃላይ 2ሺህ516 የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸዋል። እንዲሁም 3ሺህ945 የክላሽ፣ 2ሺህ324 የሽጉጥ፣ 1ሺህ563 የብሬን ጥይቶች በጥቅሉ 7ሺህ832 የተለያየዩ የጦር መሳሪያ ጥይቶች ወደ አገር ውስጥ ለመግት ሲጓጓዝ መያዙን ተናግረዋል። በሰሜን ጎንደር ገንዳ ውሃ በአደጋ ምክንያት የተገለበጠ የነዳጅ ጫኝ ቦቴ ተሽከርካሪን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አቅጣጫዎች ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ በህብረተሰቡ ጥቆማና በጸጥታ አካላት አማካይነት በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ኮማንደር አይሳ ገልጸዋል። በህገወጥ መንገድ የጦር መሳሪያ ሲያጓጉዙ የነበሩ 43 ግለሰቦች በቁ­ጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሆነ የጠቆሙት ኮማንደር አይሳ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ግለሰቦች በስተጀርባ ያሉ ወንጀለኞችን ለመያዝ ማጣራት እየተካሄደ ስለመሆኑ ተናግረዋል። ከዚህ በፊት የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ይካሄድ የነበረው ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በአሁኑ ጊዜ የነዳጅ ቦቴ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም በስፋት እየተከናወነ እንደሆነ አመልክተዋል። አብዛኞቹ ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ያሉት የቱርክ ሰራሽ ሽጉጦች ሲሆኑ ለምን? ማነው የሚያስገባው?  ምንጩ የት እንደሆነና መዳረሻውን ለማወቅ ምርመራ እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ችግሩን ለመፍታት በተለያዩ መግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ በሁሉም ተሽከርካሪዎችና እቃዎች ላይ የተጠናከር ፍተሻ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል። ''በሱዳን በኩል በነዳጅ ጫኝ ቦቴዎችና በሌሎች መንገዶች ወደ  አገር ውስጥ የሚገቡ የጦር መሳሪያዎችን ለመከላከል በጋራ እየተሰራ ይገኛል'' ያሉት ኮማንደር አይሳ በድንበር አካባቢ ያሉ የጸጥታና የመስተዳደር አካላት በትብብር እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ከሱዳን የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ወንጀሉን በጋራ ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶች መኖራቸውን ገልጸው በቀጣይ ሰፊ የሆነ ውይይት ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል። የጸጥታ አካላት የሚያደርጉትን የህገወጥ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ለመከላከል የህብረተሰቡ የተለመደ ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኮማንደር አይሳ ጥሪ አቅርበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም