በምስራቅ ሸዋ 38 ኩንታል የተቀሸረ ቡና በህገ-ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ ተያዘ

60
አዳማ ጥቅምት 22/2011 ከሻሸመኔ ወደ አዲስ አባባ በህገ-ወጥ መንገድ ሲጓዝ የነበረ 38 ኩንታል የተቀሸረ ቡና በኦሮሚያ ምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ወረዳ ሲደርስ መያዙን የዞኑ ፖሊስ አስታወቀ። የዞኑ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው አለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት ቡናው የተያዘው ዛሬ ንጋት አካባቢ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-30063 አዲስ አበባ በሆነ አይሱዙ ተጭኖ ሲጓጓዝ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ አዳሚ ቱሉ ወረዳ ዋሻ ጉላ በተባለ ስፍራ ሲደርስ ነው። አሽከርካሪው እንዲቆም የተሰጠውን ትዕዛዝ ባለመቀበል ለማምለጥ ያደረገው ሙከራም በፖሊስ አባላት የመኪናው የፊት ጎማው በጥይት በመመታቱ ሲከሽፍ ለጊዜው እሱና ረዳቱ መሰወራቸውንም አመልክተዋል። የተያዘው ቡናም ግምቱ ወደ 380 ሺህ ብር እንደሚደርስ የገለጹት ኮማንደር አስቻለው ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል። ህብረተሰቡ ህገ-ወጥነትን ለመከላከል ከፖሊስ ጋር እያደረገ ያለውን ጥረት ኃላፊው አድንቀው ለወደፊቱም መሰል ድርጊቶች ሲያጋጥሙ ጥቆማዎችን በመስጠት ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም