የኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ሊቋቋም ነው-ሚኒስቴሩ

171
አዲስ አበባ ጥቅምት 22/2011 የኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ለማቋቋም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወነ መሆኑን የከተማ ልማትና ኮስትራክሽን ሚኒስቴር ገለጸ። ሚኒስቴሩ በሚቀጥሉት መቶ ቀናት ለመስራት ባቀዳቸው ተግባራት ዙሪያ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። ሚኒስትሩ አቶ ዣንጥራር ዓባይ እንዳሉት፤ ተቋሙ የሚጠበቅበትን ተልዕኮ ለመወጣት ተቋማትን የማደራጀት እንቅስቃሴ ጀምሯል። ከእንቅስቃሴዎቹ መካከል የኮንስትራክን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ማቋቋም አንዱ መሆኑን ገልጸው የመቋቋሚያ ደንብ ተዘጋጅቶ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲጸድቅ ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል። የፌዴራል የተቀናጀ መሰረተ ልማት ኤጀንሲ፣ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን፣ የከተማ ሥራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና አጄንሲ፣ የፌዴራል መሬትና መሬት ነክ ምዝገባና መረጃ  ኤጀንሲና  የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ባለሥልጣን በሚኒስቴሩ ስር የሚታቀፉ መሆኑን ነው ያብራሩት። ተቋማቱን ወደ አንድ የማደረጀት ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት አቶ ዣንጥራር የባለሥልጣኑ ማቋቋሚያ ደንብ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉም አስረድተዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የሚቋቋመው ባለስልጣን በአገሪቷ በአጠቃላይ ከጨረታ ጀምሮ እስከ ግንባታ ትግበራ ምዕራፍ ድረስ ያሉ የኮንስትራክሽን ሥራዎችን የመቆጣጠር ስልጣን ይኖረዋል። ''በአገሪቷ የሚከናወኑ ግንባታዎች በጥራት፣ በጊዜና በተበጀተው ወጪ ማጠናቀቅ ላይ ክፍተቶች አሉ'' ያሉት ሚኒስትሩ፤ ባለስልጣኑ አንድ የግንባታ ፕሮጀክት መቼ ተጀመረ? መቼ ነው የሚጠናቀቀው? ከዘገየስ እንዴት ዘገየ? ለምን ዘገየ? ምን ያህል ወጪ ወሰደ? ጥራቱስ እንዴት ነው? የሚሉትን በሙሉ ቁጥጥር እንደሚያደርግበት አብራረተዋል። በመስኩ የሙያ ብቃት ማረጋገጫና የግንባታ መሳሪያ ፍቃድ መስጠት ሌላው የባለሥልጣኑ ኃላፊነት እንደሚሆንም አመልክተዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በቀጣይም በተለይ በአዲስ አበባ ከቤት ልማት መርሃ ግብሮችና መሬት ምዝገባ ስርዓቱ ረገድ ቅልጥፍናን ለማምጣት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር ተደርጓል በሌሎች ክልሎችም በተመሳሳይ ይቀጥላል። ከስራ ተቋራጮች ማህበራትና ከዳያስፖራዎች ጋር ውይይቶችን በማድረግ የህግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎችንም ለመተግበር ይሰራል ነው ያሉት። ተጠሪ ተቋማትን በማደራጀት አንድ የጋራ እቅድ ማዘጋጀት፣ በየዘርፉ መጽደቅ የሚኖርባቸው የህግ ማዕቀፎች እንዲጸድቁ በማድረግ ወደ ሥራ ማስገባት በሚቀጥሉት አንድ መቶ ቀናት ከሚተገበሩ እቅዶች መካከል ናቸው ብለዋል። የምዝገባ ፍቃድ አገልግሎት፣ የመሬት ምዝገባ ስርዓትና የፌዴራል የስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲን ለማቀላጠፍ የተጀመሩ የሶፍትዌር ልማቶችንም በፍጥነት የማጠናቀቅ  ተግባራት እንዲሚከናወኑም አብራርተዋል። በተጠሪ ተቋማት መካከል የሥራ ድግግሞሽ ሳይፈጠር እንዴት ተናበው መስራት ይቻላል? የሚለውም ረቂቅ እየተዘጋጀ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ በመስኩ ተቋማትን ሪፎርም የማድረግ ስራ ላይም  ሰፊ ውይይት ተደርጓል ብለዋል። እቅዶችን ወደ መሬት ለማውረድ ተመሳሳይነት ያላቸው ስራዎችን ወደ አንድ የማምጣት ስራም በቀጣይ በትኩረት የሚሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም