የህዳሴ ግድብ ግዙፍ የልማት ስራዎችን በራሳችን አቅም ማከናወን እንደምንችል ማሳያ ነው... ዶክተር አቢይ አህመድ

55
አሶሳ ሚያዝያ 23/2010 ህብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ማጠናቀቅ እንደሚቻል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማሳያ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉብኝታቸውን በዛሬው እለት ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የጀመሩ ሲሆን ከሰዓታት በፊት ደግሞ በአሶሳ ከተማ አህመድ ናስር ስታዲየም በመገኘት ለከተማዋ ነዋሪዎች ንግግር አድርገዋል። በንግግራቸውም አባቶች በመስዋዕትነትና በዋጋ ያቆዩዋትን ሃገር ከስኬት ጥግ የማድረስ ትጋት ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ መሆኑን አመልክተዋል። "ሁሉም በድካሙ ልክ የሚያተርፍባት የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በአብሮነት መቆም ግድ ይላል" ብለዋል። በረፋዱ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉብኝታቸውም የግድቡ ግንባታ ሂደት ኢትዮጵያውያን የመጀመር ብቻ ሳይሆን የመጨረስም አቅማቸውን ለአለም የሚያሳዩበት እንደሚሆን ገልፀዋል። የክልሉ ህዝብም እንደተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ለግድቡ ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልና ግድቡን የመንከባከብ ድርብ ኃላፊነቱን በብቃት እንደሚወጣ ያላቸውም እምነት ገልፀዋል፡፡ ክልሉ ሰፊ የሆነ የተፈጥሮ ኃብት ባለቤት መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄ ብቻ በራሱ ሃብታም ስለማያደርግ በተለይ የወጣቱን ኑሮ ለመቀየር የክልሉ አመራር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል። በሀገራችን ያሉ ልዩነቶች አንድነታችንን ሳይፈታተኑ ወደ ተሻለ የእድገት ደረጃ ለመድረስ መስራት እንደሚገባ የገለፁት ደግሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ናቸው። በአሁኑ ውቅት በሀገሪቱ የተፈጠረውን የሠላም የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት በመጠቀም የክልሉ ህዝቦች ከድህነት ለመውጣት የሚያደርጉት ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም