ቤተ ክርስቲያኗ ለቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት እና ለአክሱም ጽዮን ቤተክርስትያን ጥገና 40 ሚሊዮን ብር መደበች

97
አዲስ አበባ ጥቅምት 21/2011 ለቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት እና ለአክሱም ጽዮን ቤተክርስትያን ሙዝየምና ወመዘክር ጥገና 40 ሚሊዮን ብር መመደቧን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን አስታወቀች። በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች በሚገኙ የኦርቶዶክስ እምነት ቤተክርስትያናት ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚደረጉትን ሙከራዎች ለመግታት መንግስት ፈጣን የመፍትሄ እርምጃ እንዲወስድም  ቤተ ክርስቲያኗ ጥሪ አቅርባለች። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላለፉት 11 ቀናት ያካሄደውን ጉባኤ ዛሬ አጠናቋል። ፓትሪያርኩ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የጉባኤውን መጠናቀቅ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ለቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት እና ለአክሱም ጽዮን ቤተክርስትያን ሙዝየምና ወመዘክር ግንባታና ጥገና ለእያንዳንዳቸው 20 ሚሊዮን ብር እንዲመደብ ጉባኤው መወሰኑን ገልፀዋል። አክለውም በአገሪቱ በአንዳንድ ክልሎች የሰው ህይወት አልፏል፣ አብያተ ክርስትያናት ተቃጥለዋል፣ የንብረት መውደምና የዜጎች መፈናቀል መከሰቱን ተናግረዋል። አሁንም ተመሳሳይ ችግሮች እንዳሉ እየተሰማ በመሆኑ አስቸኳይ የመፍትሄ እርምጃ ካልተወሰደ ችግሩ እየሰፋና እያደገ ሊሄድ ስለሚችል መንግስት ለጉዳዩ አጽንኦት ሰጥቶ እርምጃ እንዲወሰድ ጉባኤው ማሳሰቡን አቡኑ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ከሰላምና መረጋጋት ጋር በተያያዘ በአገሪቱ የሚስተዋሉትን ችግሮች ለመከላከል ቤተ ክርሰቲያኗ የበኩሏን ጥረት የምታደርግ መሆኑንም አቡነ ማቲያስ አስታውቀዋል። ቤተክርስትያኗ የምትሰጠውን ትምህረተ ወንጌል ከመቼው ጊዜ በበለጠ አጠናክራ የምትቀጥል ከመሆኑም በላይ በመጪው ህዳር የመጀመሪያዎቹ ሰባት ቀናተ በመላው ቤተክርስትያናት ጸሎተ ምህላ እንዲደረግ መመሪያ ተላልፏል። በሌላ በኩል የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ይዞታ በሆኑትና በኢየሩሳሌም ዴር ሱልጣን የሚገኙ ገዳማት ላይ አግባብነትና የሰነድ መረጃ በሌለበት ችግር እየፈጠረ መሆኑን አንስተዋል። በዚህም የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን አላስፈላጊ ሁከትና ብጥብጥ ከመፍጠር ባሻገር ገዳሙን በሚጠብቁና በሚቆጣጠሩ መነኮሳት ላይ ችግር እያደረሰ መሆኑን ገልፀዋል። ቤተክርስትያኗ በፈጠረችው ጫና ሳቢያ  ገዳማቱን ከጉዳት ለመጠበቅና ለማደስ ባለመቻሉ ገዳማቱ እየፈራረሱ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ባቀረበችው ቅሬታና በመንግስት ጥያቄ በቅርቡ እድሳት በመጀመሩም ምስጋና አቅርበዋል። የተጀመረው እድሳት በአስከፊ ጉዳት ላይ ወደሚገኙት ሁሉም የኢትዮጵያ ይዞታዎች ይዳረሳል የሚል እምነት እንዳላቸውም ፓትሪያርኩ ገልጸዋል። በጉባኤው ላይ የኤርትራና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያናት በመንፈሳዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ በቅርበት ለመስራት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር የጋራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ስምምነት ላይ ተደርሷል። በቅዱስ ሲኖዶሶቹ መካከል የተፈጠረው አንድነት ከአሁን በኋላ በአገር ውስጥና በውጭው ዓለም ያለችው ቤተክርስትያን በአንዲት ቀኖናዊት ቤተ ክርስትያን በማዕከል እንድትመራ ተወስኗል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም