በኢትዮጵያ የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ሊጀመር ነው

108
አዲስ አበባ ጥቅምት 21/2011 ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የተጀመረውን ቀጣናዊ ትስስር ለማሳካትና ነጻ የሰዎች ዝውውርን ለማረጋገጥ ከጥቅምት 30 ቀን 2011 ጀምሮ ለሁሉም የአፍሪካ አገሮች የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት እንደምትሰጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ኢትዮጵያ የቪዛ ስርዓቷን ማሻሻሏ ለቀጣናዊ ምጣኔ ኃብት ትስስር አጋዥ ከመሆኑም በላይ የቱሪስት ፍሰትን ለመጨመር እንዲሁም ለኮንፈረንስ ቱሪዝም እድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ተብሏል። የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ከአንድ ዓመት በፊት በኢትዮጵያ መንግስት የተፈቀደላቸው 37 አገሮች ሲሆኑ ደቡብ አፍሪካ ከአህጉሩ ብቸኛ አገር ነበረች። የቪዛ አገልግሎቱ የሚሰጠው በቅድሚያ በኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ክፍያ መፈፀሙ ሲረጋገጥ ብቻ ነው። የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት ላይ የተደረገውን አዲስ ማሻሻያ በተመለከተ ለአፍሪካ ኀብረት አምባሳደሮች፣ የኀብረቱ ቋሚ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች፣ ለኀብረቱ ኮሚሽን እና በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሰራተኞች ነገ ማብራሪያ ይሰጣል። በአፍሪካ ህብረት ተገኝተው ገለፃውን የሚሰጡት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ኀብረት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ወይንሸት ታደሰ ናቸው። በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ የሚሰጠው ቪዛው ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የተጀመረውን ቀጣናዊ ትስስር ለማሳካት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ አፍሪካዊያን ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡበት አዲስ የቪዛ ስርዓት ለመዘርጋትና አፍሪካውያንን ለማስተናገድ መወሰኗን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። በዚህም መሰረት የኀብረቱ መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አገሮች ዜጎች የመድረሻ ቪዛ መስጠት እንደምትጀምር መጠቆማቸውም እንዲሁ። ''አዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ ሌሎች የአለም አቀፍ ተቋማትና የዲፕሎማቲክ ማዕከል ከመሆኗም በላይ የምታስተናግደው ኮንፈረንስ  ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፤ ለአፍሪካ አገሮች የሚሰጠው የመዳረሻ ቪዛም ይህንን አጠናክሮ ለመቀጠል ያስችላል'' ሲሉ ነበር ዶክተር ሙላቱ በዚሁ ወቅት የተናገሩት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም