ብዙኃን መገናኛ የስነ ጥበብ ዘርፉን በተመለከተ የሚሰሯቸው ዘገባዎች አናሳ ናቸው - የኢትዮጵያ ቀራጺያንና ሰዓሊያን ማሕበር

122
አዲስ አበባ ሚያዝያ 23/2010 በብዙኃን መገናኛ ሽፋን የሚያገኙ የስነጥበብ ስራዎች አነስተኛ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ቀራጺያንና ሰዓሊያን ማሕበር ገለጸ። በብዙኃን መገናኛ የሚሰሩ የስነ ጥበብ ስራ ዘገባዎችና ፕሮግሞች መስፋፋት እንዳለባቸው ተጠይቋል። ስነ ጥበብን በተመለከተ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችል የምክክር መድረክ ማህበሩ ከክራውን ፐብሊሺንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ጋር  በመተባበር ለብዙሃን መገናኛ ባለሙያዎች፣ ሰዓሊያንና ቀራጺያን እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በዛሬው ዕለት አዘጋጅቷል። በውይይት መድረኩ ላይ ስነ ጥበብ እንደ ሙዚቃ፣ ቴያትር፣ ሲኒማና ሌሎች ዘርፎች በብዙኃን መገናኛ ትኩረት ባለማግኘቱ በአገር ኢኮኖሚ ግንባታ የሚጠበቅበትን ያህል ድርሻውን እንዳልተወጣ ተገልጿል። የኢትዮጵያ ቀራጺያንና ሰዓሊያን ማሕበር ስራ አስፈጻሚ አቶ ስዩም አያሌው 'ስዕል ወይም እይታዊ ጥበባት በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ቢችልም እንኳን ወደ ማሕበረሰብ የመድረስ ችግር ይታይበታል' ይላሉ። "በእኛ አገር ሰዓሊያንና ሕብረተሰቡ እጅግ የተለያዩና የተራራቁ መሆናቸው አሳሳቢ ነው" ያሉት አቶ ስዩም ብዙኃን መገናኛ በዘገባዎቻቸው አስፋፍተው ቢቀጥሉ የተሻለ ነገር መስራት እንደሚቻል ጠቁመዋል። ሰዓሊው ብቻውን ስራውን ጀምሮ የሚጨርሰው በመሆኑ ከማህበረሰቡ ጋር የሚኖረው ትስስር የላላ እንዲሆን ያደረገው መሆኑን አቶ ስዩም አስረድተዋል። 'እንደ ቴያትር፣ ሙዚቃ፣ ፊልምና ሌሎች ጥበባት በርካታ ግለሰቦችን የማያካትትና በአንድ የፈጠራ ግለሰብ ተጀምሮ የሚጠናቀቅ በመሆኑ የጥበባት መድረክና ጉባኤ የማግኘት ችግር እንዲያጋጥመው ያደርጋል' ብለዋል። ስዕልን ከሰዓሊው ፍጆታነት ወደ ሕብረተሰብ መጠቀሚያነት ለማምጣት ብዙኃን መገናኛ የሚጫዎቱት ሚና ትልቅ በመሆኑ ስነ ጥበቡን ለማስተዋወቅ መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል። 'በመንግስትና በሕብረተሰቡ በኩል ስነ ጥበብን የመረዳትና ጥበቡን የእኔ ነው ብሎ የመቀበል ክፍተት አለ' የሚሉት አቶ ስዩም፤ የማሕበረሰቡን ችግርና እውቀት ተረድቶ ስነ ውበታዊ ነገሮችን ጨምሮ ማቅረብ እንዲቻል ለማድረግ የሚዲያ ድጋፍና ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። የካፒታል ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ወይዘሮ ትእግስት ይልማ እንዳሉት፤ ከብዙኃን መገናኛ በኩል ስነ-ጥበብን በአግባቡ የመረዳትና በበቂ እውቀት ለሕብረተሰቡ የማስተላለፍ ችግር ያጋጥማል። በመሆኑም እያጋጠመ ያለውን የእውቀት ውስንነት ለመቅረፍና ጋዜጠኞች ጥልቀት ያለው የስነ ጥበብ መረጃ እንዲያደርሱ ለማድረግ የሚያስችል ስልጠናዎች ቢኖሩ ጥሩ ነው ብለዋል። ሰዓሊያን የሚያቀርቧቸውን ስራዎች ግልጽና ማሕበረሰባዊ ማንነትና ሐብትነት ሊኖራቸው እንደሚገባ የመድረኩ ተሳታፊ ጋዜጠኞች ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም