የልማት እቅዶችና ፖሊሲዎች ነባራዊ ሁኔታዎችን መሰረት ባደረጉ የጥናትና ምርመር ውጤቶች መደገፍ አለባቸው

79
አዲስ አበባ ጥቅምት 21/2011 በኢትዮጵያ የሚቀረጹ የልማት እቅዶችና ፖሊሲዎች ህዝቡ የሚኖርበትን ነባራዊ ሁኔታዎች መሰረት ባደረጉ የጥናትና ምርምር ውጤቶች መደገፍ እንደሚገባቸው የፕላንና ልማት ኮሚሽን ገለጸ። የኢትዮጵያ የልማት ምርምር ኢንስቲትዩት በሰባት ልዩ ልዩ የጥናት ግኝቶች ላይ ከከፍተኛ ባለሙያዎች ምክክር መድረክ አድርጓል። በውይይቱም የፕላንና ልማት ኮሚሽነር ዶክተር ፍጽም አሰፋ እንደገለጹት፤ የህብረተሰቡን ችግር ለመቅረፍ የሚቀረጹ የልማት እቅዶች፣ ፖሊሲዎችና ግቦች ህዝቡ የሚኖርበትን ነባራዊ ሁኔታዎች መሰረት ባደረጉ የጥናትና ምርምር ውጤቶች የተደገፉ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል ። ይህም የህብረተሰቡን  የአኗኗር ሁኔታ በመረዳት፣ ችግሮችን ለይቶ ተገቢውን እቅድ ለማውጣትና ግብዓት ለማሟላት እንዲሚያስችል ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ የልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዮሐንስ አያሌው በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ጥናቶቹ በተመረጡ በ20 የገጠር ቀበሌዎች የተሰሩ ናቸው። ጥናቶቹ የተለያዩ የገጠር ማህበረሰቦችን፣ በርካታ መለኪያዎችን፣ የህዝቡን የአኗኗር ሁኔታ፣ የባህል ቅንብር፣ ሰዎቹ የሚኖርበትን የቦታ ርቀትና ተደራሽነትን መሰረት በማድረግ የተከናወኑ ናቸው። እነዚህ ጥናቶች የፖሊሲና የፕሮግራም ክፍተት በሚስተዋልባቸው የኢኮኖሚ ሴክተር፣ በስራ ፈጠራ፣ በግብርና መስክና መሰል ችግሮች ለመቅረፍ ይውላሉ። በቀጣይም ኢንስቲትዩቱ መሰል ጥናቶች እንዲወጡ የሚያደርገውን ድጋፍና እገዛ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም