ለረግረጋማ መሬትና ዝናብ አጠር አካባቢዎች የሚስማሙ ምርጥ የሰብል ዝርያዎች ተገኙ

71
ማይጨው ጥቅምት 21/2011 በትግራይ ደቡባዊ ዞን ለረግረጋማ መሬትና ዝናብ አጠር አካባቢዎች የሚስማሙ ምርጥ የሰብል ዝርያዎች ማግኘቱን የመኾኒ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ። የማሽላ፣የሰሊጥና የጤፍ ዝርያዎቹ በአጭር ጊዜ ለፍሬ የሚበቁ፣በሽታን የመቋቋም አቅም ያላቸውና ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ናቸው። የማዕከሉ የተፈጥሮ ሃብት ምርምር የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ኃይሉ እንደገለጹት፣ማዕከሉ በራያ አላማጣ ወረዳ በ40 ተመራማሪ  ፈቃደኛ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ በዝርያዎቹ ያደረገው ምርምር ፍሬያማ ሆኗል። ዝርያዎቹ ረግራጋማ መሬት መልማታቸውን በቤተ ሙከራ ከተፈተሸ በኋላ በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ እንዲለሙ ተደርጓል ብለዋል። በረግረጋማ ውሃ በተዋጠ ማሳ ከለሙት ሰብሎች መካከል የማሽላ ዝርያዎቹ በሄክታር ከ30 እስከ 50 ኩንታል ተገኝቶባቸዋል። ሜኮ፣ ኮራና ዱከም የተሰኙ ምርጥ የቀይ ጤፍ ዝርያዎች 20 ኩንታል በሄክታር እንደሰጡ አስተባባሪው አስታውቀዋል። ዝርያዎቹን ለማልማትም ናይትሮጂን፣ፎስፎረስ፣ዚንክ፣አይረንና ሰልፈርን ያካተተ ምጥን ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ውሏል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የለማው ምርጥ የማሽላ ዘር የአገዳ ቁመትና ዘለላው በመፋፋትና በፍጥነት ፍሬ በመሙላት አቅም ከአካባቢ ዝርያ የተሻለ ሆኖ መገኘቱን አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል፡፡ በተለይ  የማሽላ ምርጥ ዝርያ የዝናብ እጥረት በሚታይበት የሁሉጊዜ ለምለም ቀበሌ ማሳ ላይ ተሞክሮ በሦስት ወራት ለምርት መድረሱን ተናግረዋል ፡፡ በተጨማሪም ማዕከሉ በአነስተኛ የዝናብ መጠን ለምቶ በአጭር ጊዜ ለምርት የሚደርሰው ''አባ ሲና'' የተሰኘ የሰሊጥ ምርጥ ዝርያ እያስተዋወቀ መሆኑንም አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡ በሰሊጥ የሚካሄደው ምርምር በዝናብ ታግዞ ከሚለማው የማሽላ ዝርያ በተጓዳኝ በማልማት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ታልሞ እንደሚካሄድም አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሰሊጥ ምርጥ ዝርያን ከማዳበሪያ ፓኬጅ ጋር በማቀናጀት በራያ አዘቦና ራያ አላማጣ ወረዳዎች በሚገኙ 20 ገበሬዎች ማሳ ላይ እየለማ ይገኛል ብለዋል፡፡ በራያ ኣላማጣ ወረዳ የጡሙጋ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዝናቡ ደርቦ የእርሻ መሬታቸው በረግራጋማ ውሃ በመሸፈኑ የዘሩትን ማሽላና ጤፍ ማሳ ላይ ይጠፋባቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ማዕከሉ ያቀረበው የማሽላ ምርጥ ዘር ግን በረግረጋማ የእርሻ መሬት ለምቶ በሶስት ወራት ውስጥ ለፍሬ መብቃቱን አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ በፊት የአካባቢ ማሽላና ጤፍ በውሃ እጥረትና በአቀንጭራ አረም ሲጠቁ እንደነበር የሚገልፁት የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አብርሃ ዝናቡ፣ ማዕከሉ ያቀረባቸው ዝርያዎች አቀንጭራ አረምን ተቋቁመው በአነስተኛ ዝናብ ውሃ ፈጥነው ምርት ሰጥተዋል ብለዋል፡፡                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም