መንግስት ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ፍትሐዊ የሆነ የትምህርት ተደራሽነት ለማምጣት ሲሰራ ቆይቷል

68
አዲስ አበባ ግንቦት 14/2010 መንግስት ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ፍትሐዊ የሆነ የትምህርት ተደራሽነትን ለማምጣት ሲሰራ መቆየቱን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። የተደራሽነት ፖሊሲው በተጨባጭ በከፍተኛ ትምህርት መስክ ለውጥ በማምጣት በአገሪቱ ዘለቄታዊ የሕዳሴ ጉዞ እንዲረጋገጥ ማስቻሉ ተገልጿል። በአሁኑ ወቅት የትምህርት ተደራሽነትን ከማስፋት ጎን ለጎን ጥራትን ለማምጣትና ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት የስርዓተ ትምህርት ማሻሻያ ፕሮግራሞች እየተካሔዱ መሆኑ ተገልጿል። ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንዳሉት፤ በአገሪቱ ከ23 ዓመት ወዲህ የትምህርት ሽፋኑን ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት በአሁኑ ወቅት 29 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ ባለው ደረጃ በትምህርት ገበታ ላይ እንዲገኙ አድርጓል። በርካታ ዜጎች የመማር ዕድል ማግኘታቸው የአገሪቱን የተማረ የሰው ኃይል ፍላጎት ለማሟላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል። መንግስት በሁሉም አካባቢዎች የዜጎችን የመማር እድል በማረጋገጥና የትምህርት ተቋማት እንዲከፈቱ በማድረግ ተደራሽነት ላይ ሲሰራ መቆየቱን ሚኒስትሩ አንስተዋል። በአሁኑ ወቅት ከ38 ሺህ በላይ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ከ1ሺህ በላይ የግልና የመንግስት የቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዲሁም 50 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መኖራቸውን ገልጸዋል። በአገሪቱ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተደራሽነት ላይ መንግስት ሲሰራ የቆየ ሲሆን ከነዚሁ ተቋማት የሚወጡ ዜጎች እስከ ወረዳ ባለው መዋቅር አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አብራርተዋል። የተቀረጸው የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ በከተማና በገጠር ያለውን የተደራሽነት ልዩነት በመፍታት ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ ማስቻሉን ዶክተር ጥላዬ ተናገረዋል። የከፍተኛ ትምህርት እና የቴክኒክና ሙያ ስልጠና የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትሩ የሚሰለጥነው የሰው ኃይል የመንግስት ተግባራትን ለማስፈጸም ብቻ ሳይሆን ለግሉ ዘርፍ እድገት የማይተካ ሚና እንደሚያበረክትም አስረድተዋል። መንግስት የዜጎችን መብት ለማረጋገጥ በተለያየ ደረጃ በ51 የአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት እንዲሰጥ ያደረገ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረጉንም ገልጸዋል። የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲው በተተገበረባቸው ያለፉት አመታት የትምህርት ጥራትና ተገቢነትን ከማረጋገጥ አንፃር በርካታ ተግዳሮቶች ማጋጠማቸውን ያስታወሱት ሚኒስትሩ ችግሮቹን ለመፍታት ስርዓተ ትምህርቱን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም