በምስራቅ ጎጃም ዞን በሰብል ዘር ብዜት ሥራ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ከምርጥ ዘር ሽያጭ ተጠቃሚ ሆነዋል

71
ደብረ ማርቆስ ጥቅምት 21/2011 በምስራቅ ጎጃም ዞን በሰብል ዘር ብዜት ሥራ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ከምርጥ ዘር ሽያጭ በሚያገኙት ገቢ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታወቁ። በጎዛመን ወረዳ እነራፋ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ልብሞኝ ቸሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በቢራ ገብስ ዘር ብዜት ሥራ በመሳተፍ ከምርት ሽያጭ ያገኙት ገቢ ኑሯቸውን በተሻለ ለመምራት እያገዛቸው መሆኑን ተናግረዋል። ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ በዘር ብዜት ስራው እየተሳተፉ መሆናቸውን ጠቁመው፣ አምርተው ለአማራ ምርጥ ዘር ድርጅት ከሚያስረክቡት የዘር ሽያጭም በየዓመቱ ከ10 ሺህ ብር በላይ ትርፍ እያገኙ መሆናቸውን ገልፀዋል። "ከምርጥ ዘር ሽያጭ ከማገኘው ገቢ በተጨማሪ ምርጥ ዘሩን ለግል የእርሻ ስራዬ በመዋል ያለብኝን የዘር አቅርቦት እጥረት መፍታትና ምርታማነቴን ማሳደግ ችያለሁ" ሲሉም ገልጸዋል። በ2010/2011 የመኸር ወቅት በአንድ ሄክታር ተኩል መሬት እያለሙት ካለው የቢራ ገብስም የተሻለ ገቢ አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ ነው የገለጹት። በደብረ ኤሊያስ ወረዳ የጓይ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሁነኛው ረታ በበኩላቸው በዘር ብዜት ሥራ መሳተፍ ከጀመሩ አራት ዓመታት እንደሆናቸውና የሚያገኙት ገቢም በየጊዜው እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል። በአንድ ሄክታር መሬት የስንዴና የበቆሎ ዘር ብዜት ሥራ በማከናወን ከመደበኛው ገበያ በኩንታል በ400 ብር ጭማሪ ለአማራ ምርጥ ዘር ድርጅት በማስረከብ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደጋቸውን ገልጸዋል። በምስራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የዘር ብዜት ባለሙያ አቶ አባይነህ ውበት በበኩላቸው በየዓመቱ በአርሶ አደሩ ዘንድ የሚገጥመውን የምርጥ ዘር እጥረት በራስ አቅም ለመፍታት የብዜት ሥራው በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። የዘር ብዜት ሥራው የአርሶ አደሩን የዘር ጥረት ከማቀለሉ አልፎ ለገበያ የሚሆን ትርፍ ምርት እንዲያመርቱ በማድረግ ተጨማሪ ገቢ እያስገኘላቸው መሆኑንም አመልክተዋል። እንደ አቶ አባይነህ ገለጻ በተያዘው የመኽር ወቅት ምርጥ ዘር የማባዘት ሥራው በ3 ሺህ 200 ሄክታር መሬት ላይ በሰለጠኑ አርሶ አደሮች፣ በባለሃብቶችና በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ  እየተከናወነ ይገኛል። "በቢራ ገብስ፣ ሽምብራ፣ በቆሎ፣ ቦለቄ፣ ባቄላና ጤፍ ሰብሎች እየተባዛ ከሚገኘው መሬትም ከ128 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል" ብለዋል አቶ አባይነህ። የሚሰበሰበው ምርት በ2011/2012 የመኽር ወቅት ጥቅም ላይ ሲውል ከ437 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለመሸፈን እንደሚያስችልም ባለሙያው አስረድተዋል። የደበር ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሲስተር ገነት ደጉ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከምርምር የወጡ የሰብል ዘሮችን በማላመድና በማባዛት ለአርሶ አደሩ እንዲሰራጭ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅትም በ30 ሄክታር መሬት ጎሻ የተባለ የባቄላ ዝርያ በማስመጣት በአርሶ አደሮች ማሳ የማላመድ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ግልጸው ዘሩ በቀጣይ ለአርሶ አደሮች እንዲደርስ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል። በዞኑ በ2009/2010 የመኽር ወቅት ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር በማባዛት ለተያዘው የመኽር እርሻ ጥቅም ላይ እንዲውል መደረጉ ታውቋል ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም