የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ብድርና ድጋፍ ሊያደርግ ነው

75
አዲስ አበባ  21/2011 የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት ለማፋጠን የሚያስችል የ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ብድርና ድጋፍ ሊያደርግ ነው። በዋሺንግተን የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ትናንት ባካሄደው ስብሰባ ለኢትዮጵያ የ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍና ብድር ማጽደቁን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። ከጸነደቀው ገንዘብ 600 ሚሊዮን ዶላሩ ድጋፍ ሲሆን 600 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ ብድር እንደሆነም ተገልጿል። የኢትዮጵያ መንግስት እያደረገው ላለው የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊና ማሻሻያዎች በጠየቀው የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ በጠየቀው መሰረት ባንኩ ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ የሚደረገው ድጋፍና ብድር ቀጥታ መንግስት ለቀረጻቸው መርሃ ግብሮችና ላቀዳቸው ማሻሻያዎች እንደሚውልና በሶስት ዋና ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር የባንኩ ከፍተኛ የፋይናንስ ዘርፍ ባለሙያ ናታሊያ ማይሌንኮ ገልጸዋል። የፋይናንስ ዘርፉን ልማት ለማሳደግ፣ የፋይናንስ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን እና የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ማሻሻል ላይ ብድሩና ድጋፉ እንደሚውል ተናግረዋል። ብድርና ድጋፉ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ትብብርን በማሳደግ በመንግስት ስር የሚገኙ የቴሌኮም፣ የሀይልና የሎጂስቲክ ዘርፎችን አቅም ብቻ ማጎልበት ሳይሆን የግሉ ዘርፍ አቅም በማሳደግ ኢትዮጵያ ለልማት ለምታወጣው ፋይናንስ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል። ቁልፍ በሚባሉት ዘርፎች የሚደረገው ድጋፍ ተቋማዊ መዋቅርን ማስተካከል፣ ከፍተኛ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠትና ደካማ የማስፈጸ አቅምንና አግባበብ ያልሆኑ የስራ ወጪዎችን በመቀነስ የፋይናንስ አቅምን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት እንደሚረዳም ተናግረዋል። ይህም ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንድትስብና የኤክስፖርት ገቢዋን ለማሳደግ እንደሚጠቅማት ሚስ ናታሊያ አስረድተዋል። በተጨማሪም ብድሩና ድጋፉ ህብረተሰቡ በማህበራዊ መስኮች ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ ግልጽነትና ተጠያቂነት ለማስፈንና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወሳኝ ሚና ያላቸው በመንግስት ስር የሚገኙ ፋብሪካዎች አስተዳደራዊ አቅም በማሳደግ ቁልፍ የሚባሉ የህዝብ እቃዎችና አገልግሎት በሚፈለገው ጊዜ እንዲደርሱም ለሚሰራው ስራ ይውላል ብለዋል። መንግስት ኢትዮጵያን የእድገት ጎዳና የሚያጠናክሩ ተጨባጭና ጠንካራ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሆነ የሚገልጹት ደግሞ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ሚስ ካሮሊን ተርክ ናቸው። ብድሩና ድጋፉ መንግስት ተወዳዳሪነትን ለማሻሻል፣ ወጪ ንግድን ለማሳደግ፣ የስራ እድል ፈጠራና ሁሉን አሳታፊ የሆነ እድገት እንዲኖር እየሰራ ያለውን ስራ የሚደግፍ እንደሆነ ተናግረዋል። የፋይናንስ ድጋፍና ብድር የዓለም ባንክ የከፋ ድህነት ማስወገድና የጋራ የሆነ ብልጽግናን የማሳደግ ሁለት መንታ ግቦችን መሰረት ያደረገ እንደሆነም ባንኩ አስታውቋል። ብድርና ድጋፉ ባንኩ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው የትብብር ማዕቀፍና የኢትዮጵያ የልማት ስትራቴጂ ጋር የተያያዘ እንደሆነም አመልክቷል። የዓለም ባንክ የአፍሪካ ቀጠና ምክትል ፕሬዚዳንት ሃፌዝ ጋኔም ሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በነበራቸው ቆይታ በመስኖ ግብርና ማስፋፋት፣ በትምህርት ዘርፍና በዲጂታል ኢኮኖሚ የተጠናከረ ስራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረው ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወቃል።         ---END---      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም