ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ለማብሰር በተዘጋጀው ስነስርዓት ላይ ለመታደም ወደ ጁባ አቅንተዋል

101
አዲስ አበባ ጥቅምት 21/2011 የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በመስከረም ወር 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተፈረመውን የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ለማብሰር በተዘጋጀው ስነስርዓት ላይ ለመሳተፍ ወደ ደቡብ ሱዳን ርዕሰ መዲና ጁባ ማምራታቸውን የፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት አመልክቷል። ዛሬ በጁባ ጆን ጋራንግ አደባባይ በሚካሄደው ስነስርዓት ላይ የደቡብ ሱዳን መንግሥትና ተፋላሚ ኃይሎች ተሳታፊ የሚሆኑ ሲሆን የተለያዩ አገሮች መሪዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። በስነስርዓቱ ላይ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅን ጨምሮ የዩጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፣ የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሀስን አልበሽር፣ የኬንያ ፕሬዝዳንት አሁሩ ኬንያት እና የሌሎች አገሮች መሪዎችና ተወካዮች ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። የጁባው ጉዞ ፕሬዝዳንቷ ከተሾሙ በኋላ ወደ ውጭ አገር የሚያደርጉት የመጀመሪያ ይፋዊ ጉብኝት ነው። በመስከረም ወር 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው 33ኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የመሪዎች ጉባኤ የደቡብ ሱዳን ሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው። ሁለቱ ተቀናቃኝ ኃይሎች ስምምነቱን ከመፈራረማቸው በፊት በነበሩ ሶስት ወራት በሱዳን ካርቱም ወደ ሰላም ለመምጣት ድርድር ሲያደርጉ ቆይተው በኢጋድ ስብሰባ ላይ የሰላም ስምምነቱን ተፈራርመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም