ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የቡድን 20 አባል አገሮች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረቡ

65
በርሊን ጥቅምት 20/2011 የቡድን 20 አባል አገሮች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ እንዲሳተፉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከጀርመን መራሂተ-መንግስት አንጌላ መርክል ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ በርሊን እየተካሄደ ባለው የቡድን 20 አገሮች የአፍሪካ ትብብር መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። የትብብር መድረኩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ11 የአፍሪካ አገሮች ተጨማሪ የኢኮኖሚ ድጋፍ በማድረግ፣ በመሰረተ-ልማት፣ በኢንቨስትመንትና ንግድ፣ በፋይናንስ ስርዓት ማሻሻልና ሌሎች ትብብሮች ላይ ያተኮረ ነው። በዛሬው እለት በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን በተካሄው መድረክም የጀርመን መራሂተ-መንግስት አንጌላ መርክል፣ የሩዋንዳው ፕሬዚዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ፖል ካጋሜ፣ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲንና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃመትን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች መሪዎች ተሳትፈዋል። ዶክተር አብይ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር ''የቡድን 20 አባል አገሮች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በስፋት እንዲሳተፉ ትፈልጋለች'' ብለዋል። የጀርመኗ መራሂተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል በበኩላቸው ጀርመን ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያላትን የንግድ ትስስር ለማሳደግ አስፈላጊውን ትብብር እንድምታደርግ ገልጸዋል። በተመሳሳይ የሩዋንዳው ፕሬዚዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ፖል ካጋሜ ይህ አይነቱ መድረክ በአፍሪካ እየታየ ያለውን የልማት እንቅስቃሴ ወደ ላቀ ደረጃ ለማራመድ ከፍተኛ ሚና እንዳለውና በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የሚታየውን የለውጥ ጅማሬ ማበረታታት እንደሚገባ ተናግረዋል። የቡድን 20 አባል አገሮች የአፍሪካ ትብብር መድረክ የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ለማጠናከርና ለማበረታታት የተጀመረ ሲሆን የአፍሪካ አገሮች የኢኮኖሚና የፋይናንስ መዋቅራቸውን ሳቢ በማድረግ የግሉ ዘርፍ በኢንቨስትመንት በስፋት እንዲሰማራ የሚደግፍ መርሃ ግብር ነው። በአሁኑ ወቅት 11 የአፍሪካ አገሮች የመድረኩ አባል ሲሆኑ ኢትዮጵያ አንዷ ናት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም