በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ 16 ዞኖች ለቁም እንስሳት ህገ ወጥ ንግድ የተጋለጡ መሆናቸው ተገለጸ

129
አዳማ ግንቦት 14/2010 በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ 20 ዞኖች መካከል 16ቱ ለቁም እንስሳት ህገ ወጥ ንግድ መጋለጣቸውን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ገለጸ። በቁም እንስሳት የሚካሄደውን የኮንትሮባንድ ንግድ በመቆጣጠር የሚያዙ እንስሳት የሚቆዩበት 22 ጣቢያዎችን ለመገንባት ዝግጅት መደረጉም ተመልክቷል። በኦሮሚያ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወርቁ ጫላ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ከምትልከው የቁም እንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች መካከል ክልሉ ከ60 እስከ 70 በመቶ ድርሻ አለው። "በክልሉ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ከሚገኙባቸው 20 ዞኖች መካከል 16ቱ ለህገወጥ የቁም እንስሳት ንግድ የተጋለጡ በመሆናቸው አገሪቱ፣ ክልሉም ሆነ አርብቶ አደሩ የሀብቱን ያክል ተገቢ ጥቅም እያገኙ አይደለም" ብለዋል። በተለይ ከጎረቤት አገራት በድንበር የሚዋሰነው አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ለኮንትሮባንድ የቁም እንስሳት ንግድ የመጋለጥ ስጋቱ እየጨመረ መምጣቱን ነው የገለጹት። በእዚህም ክልሉ የተቀናጀና የተጠናከረ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችለውን አሰራር ለመዘርጋት በስፋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አቶ ወርቁ አመልክተዋል። ህገ ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ አገሪቷን የውጭ ምንዛሬ ከማሳጣቱም ባሻገር በኮንትሮባንድ የሚወጡት የቁም እንስሳት ደረጃቸውና ጤንነታቸው ያልተጠበቀ በመሆኑ በተቀባይ አገራት ዘንድ የኢትዮጵያ ስምና ንግድ እንዲበላሽ ምክንያት መሆኑን አቶ ወርቁ ተናግረዋል። እንደዳይሬክተሩ ገለጻ ኮንትሮባንድ የቁም እንስሳት ንግዱን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል የተያዙት እንስሳት የሚቆዩበት የተመቻቸ ማረፊያ፣ የሚበሉት መኖና የሚጠጡት ውሃ አለመኖር በዋናነት ይጠቀሳሉ። አቶ ወርቁ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ችግሩን ለመፍታት ከግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር በተገኘ የ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ 22 የእንስሳት ማቆያ ጣቢያዎች ለመገንባት ዝግጅት ተደርጓል። በቢሮው የቁም እንስሳትና እንስሳት ተዋፅኦ  ዳይሬክተር አቶ ለማ አጀመ በበኩላቸው የኦሮሚያ ክልል 23 ነጥብ 8 ሚሊዮን የዳልጋ ከብት፣ 9 ነጥብ 5 ሚሊዮን በጎች፣ 8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ፍየሎችና 300 ሺህ ግመሎች ቢኖሩትም በህገወጥ እንቅስቃሴው እየተጎዳ መሆኑን ገልጸዋል። የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴውን በቅንጅት ለመግታት እንዲቻል የእንስሳት ማቆያ ከሚገነባባቸው አካባቢዎች የተወጣጡ ከ50 በላይ ባለሙያዎች የተሳተፉበት የአንድ ቀን የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሔዷል። በምክክር መድረኩም ህገወጥ የቁም እንስሳት ንግድ እያደረሰ ባለው ጉዳት ላይና በመፍትሄው ላይ በዝርዝር ውይይት ተደርጓል። የመድረኩ ተሳታፊዎችም የእንስሳት ማቆያ ጣቢያዎች ግንባታ ሥራን በማፋጠን የቁጥጥር ስራውን ለማጠናከር በተቀመጡ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም