የህፃናት ማቆያ ማዕከል መገንባቱ ስራችንን ተረጋግተን ለማከናወን አስችሎናል -በሃዋሳ የማእከሉ ተጠቃሚ እናቶች

196
ሀዋሳ ጥቅምት 20/2011 የህፃናት ማቆያ ማዕከል መገንባቱ ስራቸውን ተረጋግተው ለማከናወን እንዳስቻላቸው በሃዋሳ ኢዜአ ያናገራቸው የማእከሉ ተጠቃሚ እናቶች ገለፁ፡፡ በደቡብ ክልል በተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች 45 የህፃናት ማቆያ ማዕከላት መገንባታቸውን የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ገልጿል፡፡ የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ በጠራው የሴክተር ስብሰባ ለመካፈል ህጻን ልጃቸውን ይዘው ከደራሼ የመጡት ወይዘሮ የምስራች ኢርኮ እንዳሉት የህጻናት ማቆያ ማዕከሉ ተረጋግተው ስብሰባውን እንዲካፈሉ አስችሏቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ለስብሰባም ሆነ ለስልጠና ወደ ሃዋሳ በሚመጡበት ወቅት ህጻን ልጅ ይዘው ለመምጣት ይቸገሩ እንደነበርና አንዳንዴ አዳራሽ ውስጥ ይዘው በመግባት ህጻኑ ሲያለቅስ ይሳቀቁ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አሁን ግን በማዕከሉ የተሟላ የህጻናት መጫወቻና ማረፊያ አልጋ ስላለ በእረፍት ሰዓት እየሄዱ ጡት በማምጣት ሳይሳቀቁና ሳይረበሹ ተረጋግተው ስብሰባውን መካፈል እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ በማቆያ ማዕከሉ ለህጻናቱ አስፈላጊ የሆኑ የንጽህና መጠበቂያ በመኖሩ መደሰታቸውን የተናገሩት ወይዘሮ የምስራች ይህ ለሌሎች አካባቢዎች ምርጥ ተሞክሮ እንደሚሆንና ሌሎችም መሰል ማዕከል ሊኖራቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ወይዘሮ ሰላማዊት ኤሊሶ በበኩላቸው እናቶች ልጆቻቸውን ለስድስት ወራት ጡት ማጥባት እንዳለባቸው በጤና ባለሙያዎች የተሰጠውን ምክረ ሃሳብ  ተግባራዊ ለማድረግ የወሊድ ፈቃዳቸው ሲያልቅ እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡ ይህን የእናቶች ችግር በማየት የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ያስገነባው የህጻናት ማቆያ ማዕከል ትልቅ እፎይታን የሰጠ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ለእናትም ለህጻኑም ጥቅም እንዳለው የተናገሩት ወይዘሮ ሰላማዊት ’’ተረጋግተን በስብሰባ እንካፈላለን ስራችንንም እንሰራለን ልጆቻችንም ሳይጎዱ ጡት እያገኘ ማደግ ይችላል’’ ብለዋል፡፡ ከጌዴኦ ዞን ለስብሰባ የመጡት ወይዘሮ ሰናይት በቀለ እንዳሉት የአምስት ወር ልጃቸውን ያረፉበት ቦታ ትተው ቢመጡ ተረጋግተው ስብሰባውን መካፈል እንደማይችሉ ገልፀዋል፡፡ ''የማዕከሉ መኖር ልጁን እየወጣሁ ለማየትና ጡት ለማጥባት አስችሎኛል'' ያሉት ወይዘሮ ሰናይት በማዕከሉ ህፃናትን የምትንከባከብ የማእከሉ ሰራተኛ መኖርዋንም ተናግረዋል፡፡ በደቡብ ክልል ሴቶችና ህጻናት ቢሮ የህጻናት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ባትሪያ ቦረዳ እንዳሉት ቢሮው ነፍሰጡር እናቶች የወሊድ ፈቃዳቸውን ጨርሰው ስራ ሲጀምሩ ጡት ለማጥባት የሚደርስባቸውን ችግር ለማቃለል ታስቦ ማዕከሉ ተገንብቷል፡፡ ከአንድ መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር የተገነባው ይህ የህጻናት ማቆያ ማዕከል እናቶች ጡት ለማጥባት ወደ ቤት ሲመላለሱ በስራ ላይ የሚደርስውን ጫና በማቃለልም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በ2008 ዓ.ም የተገነባው ይህ ማዕከል ከቢሮው ሰራተኞች በተጨማሪ ለስብሰባ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ እናቶች እየተገለገሉበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ አዋጅ ወጥቶለት በሁሉም የስራ ቦታዎች የህጻናት ማቆያ ስፍራዎችን ማዘጋጀት እንደሚገባ ስለታመነበት በክልል ደረጃ 45 ማዕከላት መቋቋማቸውን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም