የሶማሌ ክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የአባላትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ገለፀ

78
ጅግጅጋ  ጥቅምት 20/2011 የሶማሌ ክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በንግድ፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ የአባላቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስታወቀ፡፡ ምክር ቤቱ  ትናንት ባካሄደው 4ኛ ጠቅላላ ጉባኤው የምክር ቤቱን ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት መርጧል፡፡ ምክር ቤቱ ባካሄደው 4ኛ ጠቅላላ ጉባኤው ዶክተር ሐሰን አብዲላሂ በዴን ፕሬዝዳንት አድርጎ የመረጠ ሲሆን አቶ አብዲራህማን ሐጂ ቡርሀንን ደግሞ በምክትል ፕሬዝዳንትነት መርጧል፡፡ አዲሱ የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሐሰን አብዲላሂ በዴ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር  ምክር ቤቱ በንግድ፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ የአባላቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲራህማን ሀጂ በበኩላቸው "የክልሉ ንግድ ስራዎች በህግ አግባብ ብቻ እንዲከናወኑ ለማድረግ  የምክር ቤቱን አባላት ግንዛቤ ለማሳደግ ይሰራል" ብለዋል፡፡ በክልሉ የሚከናወኑ የንግድ ስራዎች በውድድር ላይ ተመስርተው እንዲሰሩ በመንግስት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የሶማሌ ክልል ንግድ ትራንስፖርትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ከድር አብዱራህማን ተናግረዋል፡፡ ቀደም ሲል የንግድ ስራዎች በክልሉ አመራሮች  ጣልቃ ገብነት በተመረጡ ግለሰቦች ይከናወኑ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ከድር አብዱራህማን  ይህ አይነቱ አሰራር ህግን ያልተከተለ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡ በክልሉ ሁሉም አከባቢዎች  ህግና አሰራርን በተከተለ መልኩ በንግድ ስራ ላይ ለመሳተፍ ለሚፈልጉ ዜጎች ቢሮው የንግድ ፍቃድ ለመስጠት መዘጋጀቱን አቶ ከድር ተናግረዋል፡፡ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች  ቢሮው ከምክር ቤቱ ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን  ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ በምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ  ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የአባላት ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ አወል ሽፋ ለክልል ምክር ቤቱ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ አገር አቀፍ ምክር ቤቱ የክልሉ የንግድና ዘርፍ ማህበራት መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ በሚደረገው እንቅስቃሴ  ኃላፊነቱን ለመወጣት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ በጅግጅጋ ከተማ  ወዳግ የፅዳትና ውበት ህብረት ስራ ማህበር ተወካይ አቶ ኢብራሂም ሃሩን በሰጡት አስተያየት የተመረጡ አመራሮች በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ አካላት በመሆናቸው ለምክር ቤቱም ሆነ ለአባላት ተጠቃሚነት የሚኖራቸው ፋይዳ የጎላ ነው፡፡ የምክር ቤቱ አባል የሆኑት ኢንጅነር አሰፋ ገበየሁ በበኩላቸው አዲሱ የምክር ቤት አመራር ከሌሎች ክልሎች ልምድ ለመለዋወጥ እና የአባላትን ቁጥር ከማሳደግ አንጻር ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ የምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ  ምክር ቤቱን ለቀጣይ 2 ዓመታት የሚመሩ 11 አዳዲስ የቦርድ አመራሮችን በመምረጥ ተጠናቋል፡፡ በ2003 ዓ.ም የተቋቋመው የሶማሌ ክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በአሁኑ ሰዓት የአባላቱን ቁጥር  ከሶስት ሺህ በላይ ማድረሱን ከመድረኩ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም