የጸገዴ ወረዳን ከከተማ ንጉስ የሚያገናኝው የአስፋልት መንገድ በመበላሸቱ መቸገራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለፁ

1739

መቀሌ ጥቅምት 20/2011 በትግራይ ምእራባዊ ዞን የጸገዴ ወረዳን ከከተማ ንጉስ የሚያገናኝው የአስፋልት መንገድ በመበላሸቱ  መቸገራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን በበኩሉ የመንገዱ ጥገና ስራ በቅርብ ቀናት እንደሚጀመር ገልጿል።

የከተማ ንጉስ ነዋሪ አቶ ሽሙዬ ወልዱ እንዳሉት መንገዱ በጎርፍ ናዳ ምክንያት ተበላሽቶ ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ የተሽከርካሪን እንቅስቃሴ እያስተጓጐለ ነው፡፡

ይህም በእለት ከእለት እንቅስቃሴያቸው ላይ ተጽእኖ እየፈጠረባቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

”በመንገዱ አነስተኛ ተሽከርካሪዎች ካለሆኑ በስተቀረ ከ30 ኩንታል በላይ የመጫን ጉልበት ያላቸው ተሸከርካሪዎች ማስተናገድ ስለማይችል የንግድ ስራዬን ለማከናወን ተቸግሬአለሁ” ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ ኪሮስ ሃይሉ ናቸው።

በችግሩ ምክንያት ሸቀጣ ሸቀጦች፣ የህንፃ መሳሪያዎችና ሌሎች ዕቃዎችን ለማጓጓዝ ባለመቻላቸው በንግድ ሰራቸው ላይ ችግር እንደተፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡

የጸገዴ ወረዳ አርሶ አደር ኪዱ ገብሩ በበኩላቸው የተደረመሰው መንገድ የቁም እንስሳትንም ወደ ጉድጓድ በማስገባት አደጋ እያደረሰባቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ሁለት ከብቶቻቸው ወደ ተደረመሰው ጉድጓድ ገብተው እንደሞቱባቸውም አርሶ አደሩ ገልፀዋል፡፡

ከዓዲ-ረመፅ ከተማ ወደ ከተማ ንጉስ መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ የነበሩ አቶ ጸጋይ ገብረተክለ በበኩላቸው በመንገዱ መበላሸት ምክንያት አገልግሎት መስጠት ማቋረጣቸውን ገልጸዋል።

የፀገዴ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሰንበቱ መንገሻ የተበላሸው መንገድ ዳገት፣ ቁልቁለትና ጠመዝማዛ የበዛበትና እስከ ጥር ወር ድረስም ጉምና ዝናብ የማይለየው በመሆኑ ለተሽከርካሪዎች እጅግ ፈታኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክትል አስተዳዳሪዋ እንዳሉት፣ መንገዱ ከሁለት ዓመት ያልበለጠ አገልግሎት ሳይሰጥ ለብልሽት መዳረጉ ”በጥራት ጉድለት ምክንያት ነው” የሚል ግምት እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡

መንገዱን ያስገነባው የፌደራል መንገዶች ባለስልጣን የችግሩን ምክንያት በአግባቡ አጣርቶ አፋጣኝ ጥገና እንዲያደርግላቸውም ጠይቋል።

የወረዳው አስተዳደር መንገዱ እንዲጠገን ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተደጋጋሚ ቢጠይቅም እስካሁን አዎንታዊ ምላሽ እንዳላገኙ የተናገሩት ደግሞ የወረዳው የኮንስትራክሸን፣ መንገድና ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የልሴ ካሳዬ ናቸው።

በኢትዮጰያ መንገዶች ባለስልጣን የጎንደር ዲስትሪክት ኃላፊ አቶ ኤፍሬም አበራ ስለጉዳዩ ተጠይቀው፣ መንገዱ በናዳ ምክንያት ከፍተኛ የመደርመስ አደጋ እንደደረሰበት ተናግረዋል።

መንገዱን ለመጠገን ማሽነሪዎች ወደ ስፍራው እየተጓጓዘ ሲሆን በሚቀጥሉት 15 ቀናት ውስጥ የጥገና ስራው እንደሚጀመር ገልፀዋል፡፡

ከጸገዴ ወረዳ መገንጠያ – ከተማ ንጉስ ያለው 22 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው በ2009 ዓ.ም መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡