ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ፎረም ነገ በፓሪስ ይካሄዳል

56
አዲስ አበባ ጥቅምት 20/2011 -18ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ፎረም ነገ በፈረንሳይ ርዕሰ መዲና ፓሪስ ይካሄዳል። ፎረሙ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንና የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት (ኦኢሲዲ) በየዓመቱ የሚያዘጋጁት ሲሆን የፈረንሳዩ የልማት ድርጅት(ኤኤፍዲ) ከሁለቱ ተቋማት በትብብር ፎረሙን ያዘጋጃል። ውይይቱ በዋነኛነት የአፍሪካ የነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ላይ እንደሚያተኩር የአፍሪካ ህብረት በድረ-ገጹ አስፍሯል። በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ እየተካሄዱ ያሉ ዋና ለውጦች ላይ ውይይት እንደሚደረግና የተሻሉ ፖሊሲዎች እንዴት ለውጡን መደገፍ ይችላሉ በሚለው ጉዳይ ላይ ምክክር ይደረጋል ተብሏል። የአፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የስራ ዕድልና ፈጠራ፣ የስደተኞች ጉዳይና የልማት አጀንዳዎች ፎረሙ ሌሎች ትኩረት የሚያደርግባቸው ጉዳዮች ናቸው። በተጨማሪም ሶስተኛው ዙር የአፍሪካ የገቢ አሰባሰብ ጥናት በፎረሙ ላይ ይፋ የሚደረግ ሲሆን ጥናቱ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ1990 እስከ 2016 ድረስ 21 የአፍሪካ አገራት የሰበሰቡትን የገቢ መጠን የሚያሳዩ መረጃዎችና ሰነዶች ላይ መሰረት ማድረጉን ኮሚሽኑ አስታውቋል። የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት ኃላፊዎች፣ የአፍሪካ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የግሉ ዘርፍ፣ የሲቪክ ማህበራት፣ ምሁራንና ታዋቂ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በፎረሙ ላይ እንደሚሳተፉም ተገልጿል። የአፍሪካ አገሮች አህጉር አቀፍ ነፃ የንግድ ቀጠና መመስረት የሚያስችላቸውን ስምምነት ባለፈው 2010 ዓም በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደው 10ኛው የአፍሪካ ህብረት ልዩ ጉባኤ ላይ መፈረማቸው ይታወሳል። እስካሁን 49 አገራት ስምምነቱን ፈርመዋል። ከ15 እስከ 22 የሚሆኑት አባል አገራት ስምምነቱን በአገራቸው ህግ አውጪ አካል ወይም ፓርላማ ከጸደቀ በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆን ይጠበቃል። የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2020 የአፍሪካን አገራት የንግድ ልውውጥ በ52 በመቶ እንደሚጨምረው የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም