ከፍተኛ የእርጥበት መጠን በሚያገኙ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ተሰጠ

67
አዲስ አበባ ግንቦት14/2010 ከፍተኛ የእርጥበት መጠን ሊያገኙ በሚችሉ የአገሪቱ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችል ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስጠነቀቀ። ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ በሚቀጥሉት 10 ቀናት በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚኖረው የደመና ሽፋን እንደሚጨምርና ይህን ተከትሎ የዝናብ መጠኑ ሊጨምር ይችላል። በዚህም መሰረት ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ጂማ፣ ምዕራብና ምስራቅ ሸዋ፣ ምዕራብና ምስራቅ ሀረርጌ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል። አዲስ አበባ ከተማ፣ ከአማራ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም፣ በጎንደር የተለያዩ ዞኖች፣ በባህርዳር ዙሪያ፣ እንዲሁም  በትግራይ፣ በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሱማሌ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው ኤጀንሲው በመግለጫው አትቷል። የተቀሩት የአገሪቱ አካባቢዎች ደረቅ ሆነው እንደሚሰነብቱ ኤጀንሲው አስታውቋል። ቀደም ብለው የእርሻ እንቅስቃሴ ለጀመሩ አካባቢዎች የሚገኘው እርጥበት የጎላ ጠቀሜታ ቢኖረውም ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችልም ከፍተኛ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ ኤጀንሲው አስጠንቅቋል። በመሆኑም በሚቀጥሉት 10 ቀናት በአብዛኛው አዋሽ፣ አባይ፣ ባሮ፣ አኮቦ፣ የላይኛውና መካከለኛው ገናሌ ዳዋ፣ ዋቢሸበሌና የኡጋዴን ተፋሰሶች ከፍተኛ እርጥበት ሊኖር ስለሚችል ጥንቃቄ እንዲደረግ ኤጀንሲው አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም