ፈረንሳይ በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ላይ የተጋረጠውን ችግር ለመፍታት ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት አላት- ዶክተር አብይ አህመድ

68
አዲስ አበባ ጥቅምት 20/2011 ፈረንሳይ በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ላይ የተጋረጠውን ችግር ለመፍታት ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት እንዳላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ትናንት ማምሻውን በፓሪስ ኤልሴ ቤተመንግስት ተገናኝተው አጠቃላይ የሁለቱን አገሮች ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። ዶክተር አብይ ከውይይቱ በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ፈረንሳይ እንደ ትናንትናው ዛሬም ለታሪክ፣ ለቅርስና ለእምነት ያላቸውን ወዳጅነት እንዲያሳዩ በማውሳት በዚህ ረገድ በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ላይየተጋረጠውን ችግር ለመፍታት ለፕሬዚዳንቱ ጥያቄ አቅርበውላቸው መልካም ምላሽ እንደሰጧቸው ገልጸዋል። ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፕሬዚዳንቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ከፕሬዚዳንቱ ጋር በሰላም፣ በዴሞክራሲና በልማት ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ውይይት እንዳደረጉና የአገር መከላከያ ሰራዊትንም ለማዘመንና የሰው ኃይል ለማሰልጠን ከስምምነት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል። በኢኮኖሚው ረገድ በአየር መንገድ አገራቱ ያላቸውን ስምምነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስና ከ100 ሚሊዮን ዩሮ በላይ አውጥተው የአዲስ አበባ ኤርፖርትን ለማዘመን እንደሚሰሩም ማክሮን ቃል መግባታቸውን ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚው ማሻሻያ ከዓለም ባንክ ከምታገኘው የበጀት ድጋፍ በተጨማሪ ፈረንሳይም የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነችም ነው ዶክተር አብይ ያወሱት። ፈረንሳይ ጥንታዊ ታሪክና ባህል ያላት በመሆኗ ከኢትዮጵያ ጋር በባህል፣ በእምነትና በቋንቋ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በሚቻልበት ጉዳይ ላይም መወያየታቸውን ጠቅሰዋል። ኢማኑኤል ማክሮን በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ በሚመጡበት ወቅት በበርካታ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚያደርጉም አመልክተዋል። የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው ዶክተር አብይ እያደረጉት ያለውን ማሻሻያዎችና የዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች አድንቀው አገራቸው ለዚሁ ማሻሻያ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል። በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተደረሰውን ስምምነት ፈረንሳይ እንደምታደንቅና አገራቱ በቀጠናው ብልጽግናና ሰላም እንዲኖር ለሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተናግረዋል። ዶክተር አብይ የሚያደርጓቸው ማሻሻያዎች በቀላሉ የማይታዩና ብዙ ፈተና የገጠማቸው እንደሆነ፤ እንደሁም "ማሻሻያዎቹን ለማድረግ ምን ያህል ከባድ እንደሆነም እረዳለሁ" ብለዋል። "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብርታት የሚጠይቀውን ጎዳና መርጠዋል እኛም ከጎናቸው እንቆማለን" ብለዋል ፕሬዚዳንቱ። በኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና የባህል ዘርፎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውጥ እንዲመጣ ያሳዩት ቁርጠኝነትና ያደረጉት ማሻሻያ በአገሪቷ ታይቶ የማይታወቅ እንደሆነም ነው  ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት። ዶክተር አብይ ከፈረንሳይ ዛሬ በቀጥታ ወደ ጀርመን በርሊን በማምራት ከጀርመን መራሂተ-መንግስት አንጌላ መርከልና ሌሎች የጀርመን ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር የሁለቱን አገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ይወያያሉ ተብሎም ይጠበቃል። ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1897 ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም