የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በማዕድን ዘርፍ በሚታየው ችግር ላይ ጥናት ሊያደርግ ነው

204
አዲስ አበባ ጥቅምት 19/2011 የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በማዕድን ዘርፍ የሚታየውን የአሰራር፣ የአሳታፊነትና የሙስና ተጋላጭነት ላይ ጥናት ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ። ኮሚሽኑ ዛሬ ከህዝብ ክንፍ ጋር በ2010 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና በ2011 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ምክክር አካሂዷል። ኮሚሽነር አየልኝ ሙሉዓለም እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ 'ለሙስና ተጋላጭ ናቸው' ተብለው በተለዩ ተቋማት ላይ የአሰራር፣ የአሳታፊነትና የሙስና ተጋላጭነት ላይ ጥናቶች ያካሂዳል። በማዕድን ዘርፍ የሚታየውን የአሰራር፣ የአሳታፊነትና የሙስና ተጋላጭነት ላይ የሚደረገው ጥናት ግኝት ለሚመለከታቸው አካላት የሚቀርብ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። በተቋማት ላይ የሚታዩ የጥቅም ግጭቶችን ለማስቀረትና አስቀድሞ የሙስና ድርጊትን ለመከላከል የተጀመረው የተቀናጀ አሰራር በግሉ ዘርፍም ለማካሄድ መታቀዱን ጠቁመዋል። በ2010 በጀት ዓመት ከ13 ሺህ በላይ የሀብት ምዝገባ መካሄዱን የተናገሩት አቶ አየልኝ ከተመዘገቡት ውስጥ የ80 ሰዎችን ሃብት ለማጣራት ታቅዶ የተከናወነው የ23 ሰዎች ብቻ መሆኑን ተናግረዋል። የተመዘገበውን ሀብት መጠን ለማጣራት ከፍተኛ ውጣ ውረድና እንቅፋቶች የበዙበት በመሆኑ የተመዘገበውን ሀብት ትክክለኛነት ማረጋገጥ ላይ ዝቅተኛ አፈፃፀም መታየቱን አምነዋል። የተቀናጀ የሙስና መከላከል ስትራቴጂ በ230 ተቋማት ላይ ክትትልና ድጋፍ የተደረገ ቢሆንም የተቀናጀ የሙስና መከላከል ስትራቴጂ ቀርጸው ወደ ተግባር የገቡ ተቋማት ቁጥር 46 ብቻ መሆኑን አመልክተዋል። ኮሚሽኑ በ2010 በጀት ዓመት 87 በመቶ የዕቅድ አፈፃፀምና 85 የህብረተሰብና የተገልጋዮች እርካታ መፍጠሩን የሚያሳይ ሪፖርት በምክክር መድረኩ ቀርቧል። በመድረኩ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ኮሚሽኑ ያቀረበው የአፈፃፀም ሪፖርት ከአገሪቱ ተጨባጭ ችግሮች ጋር የሚጋጭ መሆኑን ተናግረዋል። በትራንስፖርትና መገናኛ ብዙሃን ማህበራት ፌዴሬሽን የሥነ ምግባር መኮንን ወይዘሮ አያልነሽ ሐሰን እንደተናገሩት፤ ኮሚሽኑ አነስተኛ ዕቅድ አቅዶ 87 በመቶ  አፈፃፀም ብሎ ሪፖርት ማዘጋጀቱ መሬት ላይ ካለው ሀቅ ጋር የሚቃረን ነው። ''በምሰራበት አካባቢ የሚፈጠሩ የአሰራርና የሙስና ችግሮችን አሳውቀናቸው እስካሁን ድረስ ምላሽ አልሰጡንም'' ያሉት ወይዘሮ አያልነሽ ኮሚሽኑ በአገሪቱ ያለውን የአሰራርና የሙስና ብልሽት ለማጋለጥ የሚመጥን አቅም መገንባት እንዳለበት ገልጸዋል። በአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ የሥነ ምግባር መኮንን አቶ በቃሉ ከበደ በበኩላቸው ኮሚሽኑ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የሀብት ምዝገባ ቢያከናወንም የተመዘገቡት ምን ያህል እውነትነት እንዳላቸው የማጣራት አቅሙ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል። የቪዥን ኢትዮጵያ ፎር ዴሞክራሲ /ቪኢኮድ/ ዋና ዳይሬክተር አቶ ታደለ ደርሶ እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ የሚመዘግበውን የባለስልጣናት የሀብት መጠን በየጊዜው አሳውቃለሁ ቢልም ለህዝብ ይፋ አለማድረጉ ለአገሪቱ የሚመጥን ቁመና አለመፍጠሩን ያሳያል። ''በመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚገኙ የሥነ ምግባር መኮንኖች እንደጠላት እየተቆጠሩ ቢሮ እንኳን የሌላቸው ባለሙያዎች አሉ'' ብለዋል። ኮሚሽነር አየልኝ ከተሳታፊዎች በተነሱት አስተያየት ላይ በሰጡት ምላሽ እንዳሉት፤ የኮሚሽኑ አፈጻጸም የቀረበው ከዕቅዱ አንፃር ብቻ ነው። ጠንካራ አገር ለመገንባት ሙስናን መከላከል ወሳኝ በመሆኑ ሰፊ ስራ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት መንግስት ጠንካራ አቋም ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆነ የገለጹት ኮሚሽነሩ በአገሪቱ ስር የሰደደውን የሙስና ችግር ለማስወገድ የተሻለ የፀረ-ሙስና ትግል ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረ ገልጸዋል። ኮሚሽኑ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችንና ሰራተኞችን ሃብት መመዝገብ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ 150 ሺህ የሚጠጋ የሀብት ምዝገባ ያካሄደ ቢሆንም ለህዝብ ይፋ ማድረግ አልቻለም።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም