በአፍሪካ እየተስፋፋ የመጣውን የሰብል ተባይ ለመከላከል የጋራ ጥረት ይጠይቃል

100
አዲስ አበባ ጥቅምት 19/2011 አፍሪካውያን በአህጉሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን የሰብል ተባይ /የአሜሪካ መጤ ተምች/ ለመከላካል በጋራ መስራት እንዳለባቸው የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት አስታወቀ። በአፍሪካ በተለይ የበቆሎን ምርት የሚያጠቃ ጸረ- ሰብል ተባይ አስመልክቶ ዓለም አቀፍ ውይይት በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ነው። የድርጅቱ የሰብል ልማትና ጥበቃ ክፍል ዳይሬክተር ሚስተር ሃናስ ድሪየር በዚሁ ወቅት እንዳሉት የሰብል ተባዩ በአፍሪካ የደሃውን አርሶ አደር ምርት ለጉዳት እየዳረገው ይገኛል። በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ከ40 ሚሊዮን ሄክታር የሚልቅ የበቆሎ ምርት በጸረ-ሰብል ተባዩ መጠቃቱን መረጃዎች እንደሚያሳዩና ተባዩ ድንበር የማይገድበውና በአንድ ጊዜ ብዙ ምርት የሚያጠቃ መሆኑንም ጠቁመዋል። በተወሰኑ የአፍሪካ አገራት ይታይ የነበረው ተምች በአጭር ዓመታት ደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያን ጨምሮ በከፍተኛ ሁኔታ እየተዛመተ ስለሚገኝ ለዚህ  በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል። የበቆሎ ምርት ለአፍሪካውያን በተለይም ለደሃው ህብረተሰብ መሰረታዊ ምግብ እንደመሆኑ ጉዳቱ ከፍተኛ  መሆኑን ሚስተር ሃናስ ጠቁመዋል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ ፖሊሲ አውጪዎችና የግብርና ባለሙያዎች ሃብት በማሰባሰብ፣ በጉዳዩ ዙሪያ የተሻለ ተሞክሮ ያላቸውን አገራት ልምድ በመቀመርና የተሰሩ ጥናቶችን ወደ ተግባር በመቀየር ሚናቸውን ሊወጡ ይገባልም ብለዋል። የዛሬው ስብሰባ ዋና ዓላማ በተለያዩ ጊዚያት በጉዳዩ ዙሪያ የተሰሩ ጥናትና ምርምሮች ወደ አርሶ አደሩ የሚወርዱበትና ወደ ተግባር በሚቀየሩበት ሁኔታ ላይ ለመምከር እንደሆነ ጠቁመዋል። በተለይ ተባዩ ቀድሞ ሳይዛመት አስቀድሞ መከላከል በሚቻልበት ጉዳይ ላይ አርሶ አደሩ በቂ ገንዛቤ እንዲያገኝ መሰራት አለበት ብለዋል። በውይይቱ ተገኝተው ሐሳብ ካነሱት መካከል ዶክተር ኢያሱ አብርሃ እንዳሉት ድንበር የማይገድበውን መጤ ተምች ለመከላከል አገራት በቅንጅትና በቅርበት ሊሰሩ ይገባል። አፍሪካ በርካታ የበቆሎ ተጠቃሚ ዜጎች ያለባትና ከምታመርተው አብዛኛው የበቆሎ ምርት  በተለያዩ ተባዮች የሚጠቃባት አህጉር ናት። በአየር መዛባት ምክንያት ከምታጣው ምርት በተጓዳኝ መጤ ተምች የሚያሳጣትን የምርት መቀነስ ለመከላከል በጋራና በቅንጅት መስራት ይጠበቅባታል ብለዋል። በኢትዮጵያ በዘንድሮ የመኸር ወቅት በ600 ሺህ ሄክታር የበቆሎ መሬት ላይ መጤ ተምች ተከስቶ ከ90 በመቶ በላይ የሆነውን መከላከል እንደተቻለም መረጃዎች ያሳያሉ። ውይይቱ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከ200 በላይ  ከተለያዩ የአፍሪካና የዓለም አገራት የተውጣጡ ባለሙያዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና ባለድርሻ አካላይ ተሳታፊ ሆነዋል። የአሜሪካ መጤ ተምች መነሻ አሜሪካ ሲሆን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ የተከሰተው በደቡብ ክልል በቤንች ማጂ ዞን መሆኑን መረጃዎች ያመለከታሉ።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም