ዓመታዊው የወርልድ ቴኳንዶ የግል የበላይነት ሻምፒዮና ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል

68
አዲስ አበባ ጥቅምት 19/2011 በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርትና አካዳሚ ሲካሄድ የቆየው ዓመታዊው የወርልድ ቴኳንዶ የግል የበላይነት ሻምፒዮና ፍጻሜውን አግኝቷል። የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ያዘጋጀው ሻምፒዮና ከጥቅምት 16 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን በወንዶች ከ 52 እስከ 80 ኪሎ ግራም በሴቶች ከ46 እስከ 67 ኪሎ ግራም በአጠቃላይ በ12 ኪሎ ዓይነት 115 ተወዳዳሪያዎች ተሳትፈውበታል። የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት አስፋው ለኢዜአ እንደገለጹት ሻምፒዮናው በወርልድ ቴኳንዶ በሚካሄዱ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያን የሚወክሉ ብቁ ስፖርተኞችን ለመመልመል የተዘጋጀ ነው። በሻምፒዮናው የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ስፖርተኞች በጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም በሞሮኮ በሚካሄደው የመላው አፍሪካ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክለው እንደሚሳተፉ ተናግረዋል። የውድድር እድል ያላገኙ ታዳጊ ወጣት ስፖርተኞችን በሻምፒዮናው በማሳተፍ ልምድ እንዲቀስሙና ራሳቸውን እንዲፈትሹ ተደርጓል ብለዋል። በጥር 2011 ዓ.ም ተመሳሳይ ውድድር የግል የበላይነት ሻምፒዮና ለማዘጋጀት እቅድ መያዙን ገልጸው ዛሬ ከተጠናቀቀው ውድድር በተሻለ ብዙ ተወዳዳሪዎችን ለማሳተፍ ጥረት እንደሚደረግም ነው አቶ ዳዊት ያስረዱት። የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ባለፉት ጥቂት ዓመታት እያደገ እንደመጣና ስፖርቱ ኢትዮጵያና በአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ እያስጠራ እንደሆነም አመልክተዋል። በየዓመቱ የሚካሄዱ የወርልድ ቴኳንዶ ውድድሮችን ቁጥር በማሳደግ ስፖርቱን ለማሳደግና ለተወዳዳሪዎች የውድድር አማራጭ መፍጠር ፌዴሬሽኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት ያለ ጉዳይ እንደሆነም ነው አቶ ዳዊት ያብራሩት። በሻምፒዮናው የመዝጊያ ቀን በሴቶች የ57 ኪሎ ግራምና በወንዶች 68 እና 74 ኪሎ ግራም የፍጻሜ ጨዋታዎች ተካሂደዋል። በ57 ኪሎ ግራም ሴቶች ይፍቱስራ ኤርሚያስ ዘውድነሽ በረከትን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች ሲሆን ዘውድነሽ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች። በእምነት ታመነና ሀና ዘነበ ተጫውተው ያመጡት ነጥብ ተመሳሳይ በመሆኑ ለሁለቱም የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል። በወንዶች 68 ኪሎ ግራም አብዱራህማን ሰፋ ሙሉጌታ ይነዳን አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ ተሻላሚ ሲሆን ሙሉጌታ የብር ሜዳሊያ አግኝቷል። ዚያድ በዛኔና ዮናስ ቀሬ በተመሳሳይ ነጥብ ጨዋታቸው በመጠናቀቁ የነሐስ ሜዳሊያ ተሻላሚ ሆነዋል። የስፖርት ቤተሰቡን ቀልብ በሳበው የ74 ኪሎ ግራም ጨዋታ አብዱልፈታ ሰፋ ዳርፈተህ አምደብርሃንን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ሲያገኝ፣ ዳርፈተህ የብር ሜዳሊያ፣ ዳዊት ዲያቆን የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል። በአጠቃላይ የውድድሩ አሸናፊዎች ከሜዳሊያ ሽልማት በተጨማሪ ከአንድ እስከ ሶስት ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች የ10፣ 5ና 3 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በወንዶች ብሩክ መገርሳ በሴቶች ቅድስት ድንበሩ ኮከብ ስፖርተኞች እንዲሁም በወንዶች ዘሪሁን ዘውዴ በሴቶች ይፍቱስራ ኤርሚያስ በሁለቱም ጾታ አዲስ የታዩ ወጣት ተፋላሚዎች በሚል ለአራቱም በተመሳሳይ የ5 ሺህ ብር ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። በወንድ ኤርሚያስ ኃይለሚካኤልና በሴት ምትኬ ሰይፈ ምስጉን ዳኛ በመባል የ2 ሺህ 500 ብር ሽልማት ያገኙ ሲሆን ለሻምፒዮናው መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ ተቋማትና ግለሰቦች የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል። የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የስራ ሃላፊዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ለስፖርተኞቹ የተዘጋጀውን ሽልማት ሰጥተዋል። በኢትዮጵያ የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት በ1970ዎቹ መዘውተር መጀመሩን መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን ስፖርቱን ለማሳዳግና ለማስፋፋት ሃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በ1995 ዓ.ም ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም