ከኢትዮ-ቴሌኮም ፈጣን አገልግሎት እያገኘን አይደለም....የሆሳዕና ከተማ ቅርንጫፍ ደንበኞች

100
ሆሳዕና ጥቅምት 19/2011 ከኢትዮ ቴሌኮም ፈጣን አገልግሎት እያገኘን አይደለም ሲሉ በድርጅቱ የሆሳዕና ከተማ ቅርንጫፍ ደንበኞች ገለጹ። ኢትዮ-ቴሌኮም በበኩሉ የደንበኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣት በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ጫና እየፈጠረበት መሆኑን ገልጿል፡፡ ከሀድያ ዞን ጎምቦራ ወረዳ አገልግሎት ለማግኘት የመጡት አቶ አበራ መኖሬ እንደተናገሩት በቅርንጫፍ መስሪያ ቤቱ ሲም ካርድ ለመግዛት  ጠዋት 3፡00 ሰዓት ላይ እንደመጡ ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ አገልግሎቱን ለማግኘት ብዙ ሰልፍ ቢኖርም በትውውቅ ለሌሎች ቅድሚያ ለመስጠት በሚደረግ ጥረት ምንም ዓይነት አገልግሎት ሳያገኙ እስከ ቀኑ 11፡00 ድረስ መቆየታቸውን ተናግሯል፡፡ በእዚህም ወደመጡበት ራቅ ያለ ወረዳ ለመመለስ ጊዜው በመምሸቱ ለትራንስፖርት እንግልት መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ " የሞባይል ቀፎ ለመግዛት ከጠዋቱ 3፡00 ላይ ወደቅርንጫፉ ቢመጣም እስከ 10፡00 ድረስ አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻለ የተናገረው ደግሞ ከሃዲያ ዞን ሶሮ ወረዳ የመጣው አቶ ካሳሁን አለሙ ነው፡፡ በመስተንግዶው አካባቢ የሚስተዋለው የትውውቅ አሰራር ደንበኞች የሚፈልጉትን አገልግሎት ፈጥነው እንዳያገኙ በማድረጉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ፈጥኖ ሊያስተካክል አንደሚገባ ተናግሯል። ከሀድያ ዞን ሶሮ ወረዳ የመጡት አቶ አዲሱ ቲሮሬ በበኩላቸው በተመሳሳይ ለሲም ካርድ ግዢ ወደቅርንጫፉ መጥተው እስከ አስር ሰዓት ድረስ ተሰልፈው እንዳልተሳካላቸው አስረድተዋል፡፡ አገልግሎቱን ለማግኘት ተጨማሪ አንድ ቀን በሆሳዕና ከተማ በማሳለፋቸው ለአልታሰበ ወጪ መዳረጋቸውንም አመልክተዋል። በኢትዮ-ቴሌኮም የሆሳዕና ዲስትሪክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ይልፋሸዋ ቤተማሪያም የደንበኞች ቅሬታ አግባብ መሆኑን ገልጸው፣ ችግሩ ቅርንጫፉ ቀልጣፋ አገልግሎት ባለመስጠቱ ሳይሆን የደንበኞች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ የተከሰተ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በአምስት ሠራተኞች ይከናወን የነበረው የደንበኞች አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በአስር ሠራተኞች ያለእረፍት እንዲሰጥ በማድረግ ቅርንጫፉ አገልግሎቱን ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ ቅርንጫፎችን በሀድያ ዞን ሶሮ ወረዳ ጊምቢቹ ከተማና ሌሎች የተጠኑ ወረዳዎች ላይ ቅርንጫፎች እንደሚከፈቱም ነው ዋና ሥራ አስኪያጇ የገለጹት፡፡’ የመደበኛ ስልክ ወርሃዊ ክፍያ በተወሰኑ ቀናት ውስጥ የሚስተናገድበትና አገልግሎቱም ብዙ ጊዜ ስለማይወስድ በእዚህ ምክንያት መጉላላት የደረሰባቸው ደንበኞች ካሉ ለማስተካከል በትኩርት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በጥቅማ ጥቅምና በትውውቅ ቅድሚያ አገልግሎት የሚሰጡ የቅርንጫፉ ሠራተኞች ካሉ ተገቢ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ወይዘሮ ይልፋሸዋ አስታውቀዋል፡፡                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም