የወጣቶችን ሁለገብ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ የሚያስችሉ ተግባራት እንዲከናወኑ ተጠየቀ

132
አዲስ አበባ ግንቦት 14/2010 ወጣቶች ሁለገብ ተጠቃሚነታቸውን ሊያረጋግጡ የሚያስችሉ ተግባራት ሊከናወኑ እንደሚገባ ተናገሩ፡፡ 27ኛው የግንቦት 20 በዓልን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ወጣቶችንና ስፖርት ቢሮ በብሔራዊ ቲያትር ከአስሩም ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ 1ሺህ500 ያህል ወጣቶችን ያሳተፈ መድረክ አዘጋጅቷል። በመድረኩ የተሳተፉ እንደገለጹት፤ ባለፉት አመታት በየዘርፉ በርካታ አበረታች ውጤቶች ቢመዘገቡም አሁንም በትኩረት መሰራት ያለባቸው ተግባራት ብዙ ናቸው፡፡ የወጣቱን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎውን ማሳደግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ በውይይቱ ተሳታፊ የሆነው ወጣት ፍጹም አክሊሉ፤ ባለፉት 27 አመታት እድገት መመዝገቡን ገልጾ፤ ወጣቱን ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ግን በርካታ ማነቆዎች መኖራቸውን ጠቁሟል፡፡ ስራ አጥነትና የሚፈጠረውም የስራ እድል የወጣቱን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል ያሉ ተግዳሮቶች የወጣቱን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩን ጠቅሷል፡፡ በየአመቱ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው ለሚወጡ ወጣቶች የሚፈጠረው ስራ ተመጣጣኝ እንዲሆን ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል። ሌላዋ የውይይቱ ተካፋይ ወጣት ብሌን አሰፋ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች የሚያገኙት ክፍያ ከየኑሮ ውድነቱ ጋር ባለመመጣጠኑ ለችግር ተጋላጭ እየሆኑ እንደመጡ ገልጻለች። የመሰረተ ልማት አገልግሎት መጓደል፣ የወጣቶች ስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላት እጥረትና ሌሎች ችግሮች እንዳሉ ወጣቶቹ በውይይት መድረኩ ላይ አንስተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው፤ በከተማዋ ባለፉት 27 አመታት የወጣቱን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ስራዎች መከናወናቸው ተናግረዋል፡፡ በተለይም በከተሞች የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስትራቴጂ በመቅረጽ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ የከተማዋን ወጣቶችን በእድገት ተኮር ዘርፎች ተሳታፊ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ ወጣቱ የሚያነሳቸው የስራ እድል ፈጠራ ውስንነት፣ የመልካም አስተዳደርና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ችግሮች አሁን መኖራቸውን ተናግረው፤ 'መንግስት ችግሮቹን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው' ብለዋል። 'ወጣቱ ከስራ ተቀጣሪነት ይልቅ ስራ ፈጣሪ መሆን ይገባዋል' ያሉት አቶ ንጋቱ፣ 'ለሚፈጠሩ የስራ እድሎችም ወጣቱ ስራን ሳይንቅ በሁሉም መስክ ውጤታማ ስራ መስራት ይጠበቅበታል' ብለዋል፡፡ የተነሱ ችግሮች ደረጃ በደረጃ መፍትሔ እንደሚሰጣቸው የገለጹት ቢሮ ኃላፊው በቀጣይ የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የተጠናከረ ስራ የሚሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም