ዓመታዊው የወርልድ ቴኳንዶ የግል የበላይነት ሻምፒዮና የሶስተኛ ቀን ውሎ

56
አዲስ አበባ ጥቅምት 18/2011 ዓመታዊው የወርልድ ቴኳንዶ የግል የበላይነት ሻምፒዮና በዛሬ የሶስተኛ ቀን ውሎ ሶስት የፍጻሜ ውድድሮች ተካሂደዋል። ሻምፒዮናው ከትናንት በስቲያ በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ መጀመሩ ይታወሳል። ዛሬም ሻምፒዮናው ሲቀጥል በሴቶች 53 እና 62 ኪሎ ግራምና በወንዶች 63 ኪሎ ግራም የፍጻሜ ጨዋታዎች ተከናውነዋል። በዚሁ መሰረት በ53 ኪሎ ግራም ሴቶች ሌሊሴ ኡፌራ ንፁህ ጌታዬን የወርቅ ሜዳሊያ ስታገኝ ንፁህ የብር ሜዳሊያ ባለቤት መሆን መቻሏን የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊት አስፋው ለኢዜአ ገልጸዋል። ቤተልሄም ብርሃኑና ልደት ስጦታው ተጫውተው ተመሳሳይ ነጥብ በማግኘታቸው ሁለቱም የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል። በ62 ኪሎ ግራም ሴቶች ደሜ ሜኤሶ ረድኤት ጌታቸውን አሸንፋ የወርቅ ሜዳሊያ ስታገኝ ረድኤት የብር ሜዳሊያ አግኝታለች በዛው የክብደት ዘርፍ ፈቲያ አባጊዲ እና እድላዊት ጥላሁን ያደረጉት ጨዋታ በተመሳሳይ ነጥብ በመጠናቀቁ ሁለቱም የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል። በወንዶች 63 ኪሎ ግራም ዘሪሁን ዘውዴ ጀማል ሀጂን አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ጀማል የብር ሜዳሊያ አግኝቷል። ገመቹ ኤፍሬምና አስረሳኸኝ መንግስቱ ተመሳሳይ ነጥብ በማግኘታቸው ሁለቱም የነሐስ ሜዳሊያ ተሸልመዋል። ሻምፒዮናው ነገ ሲጠናቀቅ በወንዶች 68 እና 74 ኪሎ ግራም በሴቶች የ57 ኪሎ ግራም የፍጻሜ ጨዋታዎች እንደሚካሄዱም ነው አቶ ዳዊት አስፋው የኢትዮጵያ ዎርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን  ፕሬዝዳንት አስረድተዋል፡፡ ከአንድ እስከ ሶስት ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች በቅደም ተከትል የ10፣ የአምስት እና ሶስት ሺህ ብር ሽልማት ያገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም